ሁለት የጃፓን ባህር ሃይል ሄሊኮፕተሮች ተጋጭተው ውሃ ውስጥ ገቡ
በአደጋው የአንድ ሰው ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ ሰባት የበረራ ቡድን አባላት ጠፍተዋል ተብሏል
በደሴቶች ይገባኛል ከቻይና ጋር የምትወዛገበው ጃፓን ከአሜሪካና ሌሎች አጋሮቿ ጋር የባህር ሃይል ልምምድ በማድረግ ላይ ትገኛለች
በልምምድ ላይ የነበሩ ሁለት የጃፓን ባህር ሃይል ሄሊኮፕተሮች መጋጨታቸው ተነገረ።
እያንዳንዳቸው አራት ሰዎችን አሳፍረው የነበሩት ሄሊኮፕተሮች ተጋጭተው ፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ መግባታቸውን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሄሊኮፕተሮቹ ውስጥ ከነበሩት ስምንት ሰዎች መካከል የአንዱ ከውሃ ውስጥ መውጣት ቢችልም ህይወቱ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፥ ሰባቱ እስካሁን አልተገኙም።
የጠፉትን ሰባት ሰዎች ለመፈለግም 12 መርከቦችና ሰባት አውሮፕላኖች መሰማራታቸው ነው የተነገረው።
“ኤስኤች-60ኬ” የተሰኙት ሄሊኮፕየሮች ከቶኪዮ 600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በቶሪሺማ ደሴት አካባቢ በምሽት ልምምድ ሲያደርጉ ከግንኙነት መስመር ውጭ መሆናቸውን የጃፓን መከላከያ ሚኒስትሩ ሚኖሩ ኪሃራ ገልጸዋል።
ጃፓን የሄሊኮፕተሮቹ ግጭት መንስኤ እስኪታወቅ ድረስ የ“ኤስኤች-60ኬ” ሄሊኮፕተር የበረራ ልምምዶች እንዲቋረጡ ወስናለች።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተጋጭተው ባህር ውስጥ ከገቡት ሄሊኮፕተሮች የበረራ መረጃ መመዝገቢያውን ማግኘታቸውም የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ እንደሚረዳ ተገልጿል።
ጃፓን 70 የሚጠጉ “ኤስኤች-60ኬ” ሄሊኮፕትሮች እንዳሏት የአሶሼትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል።
እነዚህ ሄሊኮፕተሮች ባህር ሰርጓች መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ፣ ለቅኝትና ሌሎች ተልዕኮዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ቶኪዮ በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ደሴቶች እና በምስራቅ የቻይና ባህር ከቤጂንግ ጋር የገባችበትን ፍጥጫ በፈርጣማ ወታደራዊ አቅም ለመመለስ ከ2022 ወዲህ ጦሯን እያጠናከረች ነው።
ከአሜሪካ እና ሌሎች አጋሮቿ ጋር በመተባበርም የጋራ የባህር ሃይል ልምምዶችን በተደጋጋሚ ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።