የኤምሬትስ ሄሊኮፕተር ከካርበን ብከለት ነጻ በሆነው “ዘላቂ ነዳጅ” ጉዞ አደረገች
ከብክለት የጸዳ ነዳጅ በመጠቀም የተደረገው ጉዞ በመካከለኛ ምስራቅ የመጀመሪያው ነው ተብሏል
ቭአረብ ኤምሬትስ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ከባቢ አየርን እንዳይበክል እየሰራች ነው
የአረብ ኤምሬትስ ሄሊኮፕተር ከካርበን ልቀት ነጻ በሆነው ”ዘላቂ ነዳጅ” የመጀመሪያውን የሙከራ ጉዞ አደረገች።
የአቡዳቢ አቪየሽን ከሊዮናርዶ ሄሊኮፕተርስ ጋር በመሆን ነው ሙከራውን ያደረገው።
በሄሊኮፕተሯ የኤምሬትስ የኢንዱስትሪ፣ የኢነርጂ እና ሌሎች ተቋማት መሪዎች መጓዛቸውንም የሀገሪቱ የዜና ወኪል ዋም ዘግቧል።
በባህረሰላጤውም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ የመጀመሪያ የሆነው ጉዞ ኤምሬትስ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው የአየር ብክለት እንዳያስከትል እያደረገች ያለውን ጥረት ያሳያል ተብሏል።
የአቡዳቢ አቪየሽን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበሩ ናደር አህመድ አል ሃማዲ እንደገለጹት የአቪየሽን ዘርፉን ከካርበን ብክለት ነጻ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በ”ዘላቂ ነዳጅ” የምትሰራው ሄሊኮፕተር ያደረገችው ጉዞም ይህንኑ ያሳያል ነው ያሉት።
የሊዮናርዶ ሄሊኮፕተርስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጂያን ባዮ ኮቲሎ በበኩላቸው፥ የአቪየሽን ኢንዱስትሪው የከባቢ አየር ብክለት ምንጭ እንዳይሆን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉ አመላክተዋል።
አረብ ኤምሬትስ በያዝነው ታህሳስ ወር መጨረሻ የምታስተናደው አለማቀፍ የአቪየሽን ጉባኤ ከብክለት የጸዳው (ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ) በስፋት ጥቅም ላይ በሚውልበት ሁኔታ ይመክራል።
በ”ዘላቂ የአውሮፕላን ነዳጅ” የምትሰራው “AW139” ሄሊኮፕተር በአቡዳቢ ካደረገችው የተሳካ ሙከራ አስቀድሞ በጃፓን እና ማሌዥያ መሰል ጉዞ አድርጋለች።
የአቪየሽን ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎችን እየከወነች የምትገኘው አረብ ኤምሬትስ የአውሮፕላን ነዳጅ የካርበን ብክለት ደረጃው እንዲቀንስና ዘላቂ በሆነ ታዳሽ ሃይል እንዲተካ እየተጋች ነው ተብሏል።