በጃፓን ቶኪዮ በየቀኑ ከ800 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ እየተያዙ ሰለሆነ መንግስት እርምጃዎች ሊወስድ መሆኑ ተሰምቷል
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮሺሂድ ሱጋ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመውሰድ ምሳሌ እንደሚሆኑ ፍንጭ መስጠታቸው ተገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ መዲና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ፍላጎት እንዳላቸውም እየተገለጸ ነው፡፡ ዮሺሂድ ሱጋ ይህንን ሀሳብ ያቀረቡት በቶኪዮ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳለ ከተገለጸ በኋላ መሆኑን ሲጅቲኤን ዘግቧል፡፡
በቶኪዮ በቀን ከ800 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ በመያዛቸው ምክንያት መንግስት እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሆነም ነው የተሰማው፡፡ የጃፓን መንግስት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ጥቅም ላይ ለማዋል የማጣራት ሂደቱ ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጠው ያስታወቀ ሲሆን በየካቲት ወር ላይ ለመጀመርም ማሰቡን አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ክትባቱን በመውሰድ ምሳሌ መሆን እንደሚፈልጉ መግለጻቸውም ተዘግቧል፡፡በቶኪዮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅ ከሆነ ቀደም እንዳሉት አዋጆች አስገዳጅ ላይሆን ይችላልም ተብሏል፡፡ አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተጨማሪ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጅ ከሆነ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ጃፓን ባለፈው ወር በሀገሪቱ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውና በቫይረሱ የተያዙ የውጭ ሀገር ዜጎች እንዳይገቡባት ማገዷ ይታወሳል፡፡ የኮሮና ቫይረስ መከሰት በቶኪዮ በ2020 ሊዘጋጅ የነበረውን የኦሊምፒክ ጨዋታ ወደ 2021 እንዲዛወር መደረጉ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2020 የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ የኮሮና ቫይረስ በመስፋፋቱ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲሰረዙ ከመወሰኑ በፊት ጀምሮ ከስፖርት አስተዳዳሪዎች ጋር ሰፊ ውይይቶችን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የጃፓን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ሙሉ ጤነኛ ሆነው ሀገራቸውን መምራት እንደማይችሉ በመግለጽና ሕዝባቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ከኃላፊነት መነሳታቸው የሚታወስ ነው፡፡