
በወር 5 ሺህ ጠርሙሶች ብቻ የሚመረቱ ሲሆን ወሀው ከንጽህናው ባሻገር የሚቀርብባቸው ቅንጡ ጠርሙሶች ለዋጋው ውድነት ምክንት ናቸው ተብሏል
በምድር ላይ ለመኖር አስፈላጊ ከሚባሉ የተፈጥሮ ስጦታዎች መካከል ውሀ አንዱ እና ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በመጪዎቹ አመታት ለመጠጥነት የሚያገለግል ውሀ ከነዳጅ የበለጠ ዋጋ እንደሚኖረው ቢነገርም የጃፓኑ ውሀ አምራች ኩባንያ አስቀድሞ ከፍተኛ ዋጋ በመቁረጥ እየቸበቸበ ይገኛል፡፡
“ፊሊኮ ዋተር” የተባለው በጃፓን የሚመረተው ቅንጡ ውሀ በሊትር 10 ሺህ ዶላር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
በፈረንጆቹ 2005 የተመሰረተው ኩባንያ ውሀን በተለየ መንገድ አሽጎ በማቅረብ እና ከፍተኛ የሽያጭ ዋጋን በመጠየቅ ሰዎች ለየት ያለ የቅንጦት ልምድ እንዲኖራቸው እየሞከረ ይገኛል፡፡
ኩባንያው በማዕድናት የበለጸገ ንጹህ ውሀ ማቅረብ የሚጠብቀውን ያክል ሽያጭ ሊያስገኝለት ባለመቻሉ በተራቀቀ ጥበብ ንድፍ የሚሰሩ ማሸጊያ ጠርሞሶችን በመስራት ውሀውን ለገበያ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የውሀ ማሸጊያ ጠርሙሱ ልክ እንደ ጥበብ ስራ ለብቻው እየተሸጠ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
በተወሰነ መጠን ምርት የሚዘጋጀው “ፊሊኮ ጌጣጌጥ ውሃ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ውሀ ዛሬ ላይ በአለም ላይ ከሚፈለጉ የቅንጦት የታሸገ የውሃ ብራንዶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡
የኢንዱስትሪ እና የግብርና እንቅስቃሴዎች ከሚደርግባቸው የጃፓን አካባቢዎች ራቅ ካለ ስፍራ የሚመረተው ውሀ በንጽህናው እና በከፍተኛ ማዕድን ይዘቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ የምንጭ ውሃው በተፈጥሮ የእሳተ ገሞራ አለት ውስጥ ተጣርቶ ማለፉ የተለየ አዲስ ጣዕም እንዲላበስ አስችሎታል፡፡
በተጨማሪም ውሀው ተፈጥሯዊ ይዘቱን እንዳያጣ በአነስተኛ የማቀነባበርያ እና የማጣርያ ሂደቶች ውስጥ እንዲያልፍ መደረጉ ተፈላጊነቱን ጨምሮታል፡፡
ነገር ግን የ”ፍሊኮ ጌጣጌጥ ውሃ” ንፁህነት እና ማዕድናት ለዋጋው በዚህ ልክ መጋነን በቂ አይደለም አምራች ኩባንያው ለእያንዳንዱ ሊትር ውሀ ማሸጊያነት የሚጠቀማቸው ጠርሙሶች በስዋሮቭስኪ ክሪስታሎች ያጌጠ፣ በወርቅ የተለበጠ እና በንጉሣዊ ምልክቶች ያሸበረቀ በእጅ የተሰራ የተራቀቀ የጥበብ ስራ ውጤት ነው፡፡
በዚህም የፍሊኮ ጠርሙስ የውሃ መያዥያ ብቻ ሳይሆን የሀብት እና የቅንጦት ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለይም በንጉሳዊ ቤተሰቦች ውስጥ እና በተለያዩ ባለጸጎች ድጎስች ላይ ውሀው ከፍተኛ ተጠቃሚዎችን አፍርቷል፡፡
የውሀውን ቅንጡነት ለመጠበቅ በሚልም ኩባንያው በወር 5ሺህ ጠርሙሶችን ብቻ በማመርት ላይ ይገኛል፡፡