በዓለማችን ካለው የሚጠጣ ውሀ ውስጥ 14 በመቶው በመኖሪያ ህንጻዎች ላይ ይገኛል
አሜሪካ ከሻወር እና ኩሽና ውሀ ፍሳሾች ቢራ ጠመቀች።
ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው ኢፒክ ክሊን ቴክ የተሰኘው ኩባንያ ከመኖሪያ ህንጻዎች ላይ ካለ ፍሳሽ ቢራ መስራቱን አስታውቋል።
እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆኑ ኩባንያው ከአፓርታማዎች የሚለቀቁ ጥቅም የሰጠ ውሀን መልሶ በማጣራት ዳግም ወደ አገልግሎት መልሻለሁ ብሏል።
የኩባንያው መስራች እና ስራ አስፈጻሚ አሮን ታርታኮቭስኪ እንዳሉት ኩባንያቸው ከመኖሪያ ህንጻዎች የሚለቀቁ የኩሽና፣ ሻወር እና መጸዳጃ ቤቶች የሚለቀቅን ውሀ በቴክኖሎጂ በማጣራት ጥሩ ጣዕም ያለው ቢራ ሰርቷል ብለዋል።
ቢራው ለመጠጥ ዝግጁ ሆኗል ያሉት ስራ አስፈጻሚው በኬሚካል እና ጸሀይ ጨረር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለሰው ልጅ ጤና ተስማሚ በሚሆን መንገድ መሰራቱንም አክለዋል።
ኩባንያው ከጀርመን ቢራ አምራች ኩባንያዎች ጋር በመቀናጀት ቢራውን እንደሰራም አስታውቋል።
የመኖሪያ አፓርታማዎች በዓለማችን ካሉ ንጹህ ውሀ መጠን ውስጥ 14 በመቶውን ይይዛሉ ያሉት ሀላፊው ይህን ያህል የውሀ መጠን በማጣራት ዳግም ወደ አገልግሎት ካልመለስን የውሀ ዕጥረት ያጋጥማል ብለዋል።
ይሁንና ህንጻዎች ከሚለቁት ቆሻሻ ውሀ የተሰራው ቢራ ለገበያ አልቀረበም የተባለ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ የአሜሪካ የንግድ ህግ ከመልሶ ማጣራት ውሀ የተሰራ ቢራ ለገበያ እንዳይቀርብ የሚከለክል የቆየ ህግ ስላላት እንደሆነ ተገልጿል።
ኢፒክ ክሊን ቴክ ኩባንያ በሳን ፍራንሲስኮ ከመኖሪያ ቤቶች ከሚለቀቁ 95 በመቶ የውሀ ፍሳሾችን መልሶ በማጣራት ዳግም አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ላይ ይገኛል ተብሏል።
በርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ጥቅም ላይ የዋለን ውሀ ዳግም በማጣራት ለንጹህ መጠጥ ማዋል የጀመሩ ሲሆን ካሊፎርኒያ፣ ቴክሳስ፣ አሪዞና፣ ፍሎሪዳ እና ዋሽንግተን ዋነኞቹ ናቸው።