ፖለቲካ
በጥይት የተመቱት የጃፓን የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ህይወታቸው አለፈ
የቀድሞው ጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ከሁለት ዓመት በፊት በጤና እክል ምክንያት ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል
ሽንዞ አቤ በምዕራብ ጃፓን ናራ በምትባል ከተማ ንግግር እያደረጉ ከሰዓታት በፊት ቆስለው ህክምና ላይ ነበሩ
በጥይት ተመትተው ቆስለው የነበሩት የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ህይወታቸው አለፈ።
ሽንዞ አቤ በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ናራ ተብላ በምትጠራ ከተማ በተሰናዳ አንድ የፖለቲካ መድረክ ላይ ከሰዓታት በፊት ንግግር በማድረግ ላይ እያሉ ከኋላ በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትተው ህክምና ላይ ነበሩ።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ሽንዞ አቤ በደረሰባቸው ጥቃት ህክምና ቢደረግላቸውም ህይወታቸውን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል፡፡
በሽንዞ አቤ ላይ ጥይት የተኮሰው ግለሰብም በፖሊስ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት ሲሆን ሽንዞ አቤም ደረታቸው ላይ የተተኮሰባቸው ጥይት ልባቸውን ክፉኛ እንደጎዳው ተገልጿል፡፡
ሺንዞ አቤ በፈረንጆቹ መስከረም 2020 ላይ በጤና እክል ምክንያት ከጠቅላይ ሚንስትር የስልጣን መንበራቸው የለቀቁ ሲሆን በጃፓን የስልጣን ታሪክ ሀገሪቱን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ቀዳሚው ሰው ናቸው።
በቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ ላይ የደረሰውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ የበርካታ ሀገራት መሪዎች ሀዘናቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።