የ‘ኳድ’ ሀገራት ለመሰረተ ልማት ግንባታ 50 ቢሊዮን ዶላር በጀት መድበዋል
የአሜሪካ፣ የጃፓን፣ የአውስትራሊያ እና የሕንድ መሪዎች ቻይና እና ሩሲያን አስጠነቀቁ፡፡
መሪዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ የቻይና እና ሩሲያን ስም ባይጠቅሱም ሀገራቱን በተደጋጋሚ በሚከሱባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡
በታይዋን ያለው ወታደራዊ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው የገለጹት መሪዎቹ፤ የዩክሬን እና ሩሲያን ጦርነት በአግባቡ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ በመግለጫው አንስተዋል፡፡
ሀገራቱ ሩሲያ ዩክሬንን ‘ወራለች’ የሚል ሃሳብ አንስተው ይህንን መከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል በመግለጫቸው፡፡
በሩሲያ ጦርነት ላይ ምላሽ መስጠት ሌሎች ሀገራት ወረራ እንዳያካሂዱ ሊያደርግ እንደሚችልም ነው ሀገራቱ ያስታወቁት፡፡ የሩሲያ ‘ዩክሬንን መውረር‘ የዓለም አቀፍ ሕግ መሰረታዊ መርሆች እንዲያሽቆለቁሉ ማድረጉንም መሪዎቹ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡
አሜሪካ፤ ታይዋንን ከቻይና ወረራ ለመጠበቅ ኃይል ልትጠቀም እንደምትችል አስታወቀች
‘ኳድ’ በሚል የሚጠሩት ሀገራት መሪዎች ባወጡት መግለጫ ሩሲያን እና ቻይናን በስም ባይጠቅሱም የጠቀሷቸው ወቅታዊ ሁኔታዎች ግን ከሁለቱ ሀገራት ውጭ አለመሆናቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል፡፡
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ሀገራትን አላግባብ መውረር፣ ሁከት መፍጠርና ወታደራዊ አቅምን ማሳየትና የሌሎችን ግዛት በሃይል ለመቀማት መሞከርን አጥብቀው እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ድርጊቶች በየትኛውም ቦታ በተለይም በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ማድረግን እንደሚቃወሙም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት፡፡
የአሜሪካ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያና ሕንድ መሪዎች ጉባዔያቸውን ካደረጉ ከሰዓታት በኋላ የቻይና እና የሩሲያ ወታደራዊ አውሮፕላኖች በጃፓንና በምስራቅ ቻይና ባህር አካባቢ ባለው የአየር ክልል ላይ ሲበሩ እንደነበርም የጃፓን መከላከያ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሩሲያን ድርጊት ሲቃወም ቻይና ግን ሩሲያን ስትደግፍ እንደነበርም ነው ሀገራቱ የገለጹት፡፡
‘ኳድ’ የሚባለው ስብስብ ውስጥ ያሉት ሀገራት በቀጠናው ላለው መሰረተ ልማት መገንቢያ የሚሆን 50 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸው ተገልጿል፡፡ በጀቱ የተመደበው ለአምስት ዓመት ሲሆን የቻይናን እንቅስቃሴ ለመከታተል እንደሚያግዝም ነው የተጠቀሰው፡፡