ለ6 አመት የአልጋ ቁራኛ የነበረው ማሌዥያዊ መንቀሳቀስ እንደጀመረ የክፉ ጊዜ ሚስቱን ፈቷል
ግለሰቡ ለአመታት ከአጠገቡ ያልተለየችውን ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሚስት ማግባቱም “ወለታቢስና ጨካኝ” አስብሎታል
እንዳገገመ አዲስ ትዳር የመሰረተው ግለሰብ በማህበራዊ ሚዲያዎች ትችቱ ቢበዛበትም የቀድሞ ሚስቱ እየተከላከለችለት ነው
ለስድስት አመታት የአልጋቁራኛ የነበረው ማሌዥያዊ ከአልጋ እንደተነሳ ያለመሰልቸት ስትንከባከበው የቆየችውን ሚስቱን ፈቷል።
መንቀሳቀስ እንደጀመረ ሌላ ሚስት አግብቶ ባለውለታውን ከቤት ማስወጣቱም መነጋገሪያ ሆኗል።
ኑሩል ስያዝዋኒ ከስድስት አመት በፊት የመኪና አደጋ የገጠመውንና መንቀሳቀስ የማይችለውን ባለቤቷን የየእለት ውሎ 30 ሺህ ለሚጠጉ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ በማጋራት ትታወቃለች።
ምግብ በቱቦ የምትሰጠው፤ ዳይፐር የምትቀይርለት፤ ገላውን የምታጥበው ኑሩል በፈታኝ ወቅት ከባሏ ጎን ነበረች።
ከስድስት አመት በኋላ መንቀሳቀስ ሲጀምር ግን የኑሩልን ስቃይ የዘነጋ የሚመስል ድርጊት ፈጽሟል።
በአስቸጋሪ የህይወቱ ምዕራፍ ሳትጠየፍ የተንከባከበችውን ሚስቱን ፈትቶ አዲስ ትዳር መስርቷል መባሉ በርካቶችን አስደንግጧል።
የኑሩልን የየእለት ድካም የሚመለከቱ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ የሚስቱን ድካም ከምንም ሳይቆጥር እንደተሻለው ሌላ ሚስት ለማግባት ፍቺ መፈጸሙ አስገርሟቸው የስድብ ናዳ እያወረዱበት ነው።
ከቀድሞ ባለቤቷ አንድ ልጅ የወለደችው ኑሩል ግን ፍቺያቸውንና አዲሱን ትዳር በተመለከተ ያጋራችውን ጽሁፍ በማስወገድ ትችትና ስድቡ እንዲቆም ጠይቃለች ብሏል ኦዲቲ ሴንትራል በዘገባው።
“ሴት ልጃችን በጋራ ለማሳደግ ተስማምተናል፤ እርሱን (የቀድሞ ባለቤቷን) እና ሚስቱን መስደብና ማሸማቀቅ አይገባም” የሚል መልዕክት ብታስተላልፍም ተከታዮቿ ግን በዚህ ሃሳቧ አይስማሙም።
“የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ እንዴት ምስጋና ቢስ ይሆናል? ምን አይነት ልብ ቢኖረው ነው?” ያለ አስተያየት ሰጪ፥ የኑሩል ስያዝዋኒን የማያልቅ ደግነት አድንቋል።
በፌስቡክ የተለቀቀው መረጃ በርካቶች ጋር መድረሱን ተከትሎ የቀድሞ ባሏ እና የአዲሱ ህይወት ሊበጠበጥ ይችላል ያለችው ኑሩል ግን ይቅርታ በመጠየቅ ትችትና ስድቡ እንዲበርድ ተማጽናለች።