ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ናሚቢያ እና ኬንያ መጓዛቸው ተገለጸ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን በ2023 አፍሪካን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል
ጉብኝቱ ጂል ባይደን ቀዳማዊት እመቤት ከሆኑ በኋላ በአፍሪካ የሚያደርጉት የመጀመሪያው ጉዞ መሆኑ ነው
ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ናሚቢያ እና ኬንያ መጓዛቸው ተገለጸ፡፡
ጂል ባይደን ቀዳማዊት እመቤት ከሆኑ በኋላ በአፍሪካ የሚያደርጉት መጀመሪያው ጉዞ ሲሆን የዋይት ሃውስ እና ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል፡፡
አንድ ከፍተኛ የዋሽንግተን ባለስልጣን "የቀዳማዊት እመቤቷ የጉዞ አላማ የአሜሪካ መንግስት በአፍሪካ የሚያፈሰው መዋዕለ ንዋይ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሴቶችን እና ወጣቶችን የማብቃት ስራቸውን ለማስቀጠል ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ ጉዞው አሜሪካ መቼም ቢሆን የአፍሪካ አጋር እንደምትሆን ፕሬዝዳንት ባይደን ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው”ም ተብሎለታል፡፡
ጂል ባይደን በጉብኝታቸው ከሀገራቱ ቀዳማዊ እመቤቶች ጋር በመገናኘት በወጣቶች ተሳትፎ እና በሴቶች ማብቃት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቀዳማዊ እመቤቷ በፕሬዝዳንት ኦባማ ዘመን ጆ ባይደን ምክትል ሳሉ በኬንያ የሚገኘውን ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ (ሶማሊያውያን ስደተኞች የሚገኙበትን) ጨምሮ የተለያዩ ስፍራዎች በአምስት የተለያዩ ወቅቶች ገብኝተው ነበር፡፡
የአሁኑ የቀዳማዊ እመቤቷ ጉብኝት ለአሜሪካ-አፍሪካ ግንኙነት ይበልጥ መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡
በተለይም አሁን ባለው የዓለም አሰላለፍ ቻይና እና ሩሲያ የአፍሪካን በር ማንኳኳት በጀመሩበት ወቅት የተደረገ በመሆኑ አሜሪካ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን ወዳጅነት የምታጠናክረበትና ጥቅሞቿን ማስጠበቅ የምትችልበት አጋጠሚ መሆኑ ይገለጻል፡፡
አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣን እንደተናገሩት ግን ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪካ ያላቸው ሚና አሜሪካን ብዙ የሚያስጨንቅ ነገር አይደለም፡፡
ባለስልጣኑ "በአፍሪካ ላይ ያለን ፖሊሲ ከአፍሪካውያን ጋር በጋራ ስለምንሰራው ነገር ላይ ያተኮረ ነው" ብለዋል፡፡
"ያ ማለት አሁን ያለንበትን ወሳኝ ወቅት አናውቅም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን አሁን ቻይና በአፍሪካ ባለት ሚና ተደናግጠን ፖሊሲያችንን እያስተዋወቅን አይደለም፤ ብዙ ባለስልጣኖቻችን ስለ ቻይና ከአፍሪካውያን ጋር ይወያያሉ፥ ነገር ግን ያ የዚህ ውይይት ትኩረት ይሆናል ብዬ አላስብም” ሲሉም አክለዋል ባለስልጣኑ፡፡
የዋይትሃውስ መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ በዛሬው እሮብ እለት በናሚቢያ የጀመረው የቀዳማዊት እመቤቷ ጉብኝት እሁድ እለት በኬንያ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው አመት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደውና ወደ 50 የሚጠጉ የአፍሪካ መሪዎች በተሳተፉበት የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ዲሞክራሲን በፋይናንስ ለመደገፍና ለማጠናከር በቢሊየን የሚቆጠር ዶላሮችን ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
ፕሬዝዳንቱ በ2023 አፍሪካን ለመጎብኘት “ጓጉቻለሁ”ም ብለው ነበር በወቅቱ፡፡
ዋይት ሃውስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አፍሪካን መቼ ሊጎበኙ እንደሚችሉ እስካሁን ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም፡፡