ሩሲያ የፕሬዝዳንት ባይደንን የዩክሬን ጉብኝት “ቴአትር” ነው ስትል አጣጣለች
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዩክሬን እና ፖላንድ በተጨማሪ የኔቶ ምስራቅ እዝን ጎብኝተዋል
ምዕራባዊያን ለዩክሬን እየሰጡት ያለውን ገደብ የለሽ ድጋፍ ተከትሎ ሩሲያ የኑክሌር ጦርነት ሊከሰት እንደሚችል አስጠንቅቃለች
ሩሲያ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የዩክሬን ጉብኝት “ቴአትር” ነው ስትል አጣጣለች።
አንደኛ ዓመቱ እየተከበረለት የሚገኘው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ሲያፈናቅል የዓለም ኢኮኖሚን እና ዲፕሎማሲንም አናግቷል።
ልዩ ዘመቻ በሚል ለአንድ ሳምንት በሚል የተጀመረው ይህ በነገው ዕለት ድፍን አንድ ዓመት የሚሞላው ሲሆን ምዕራባዊያን ባንድ በኩል የምስራቅ ሀገራት ደግሞ ባንድ በኩል ሆነው የቀጥታ እና እጅ አዙር ጦርነቱ ቀጥሏል።
- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ድንገተኛ ጉብኝት እደረጉ
- ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷን አስታወቀች
ሁለቱም ወገኖች የጦርነቱን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ላይ ሲሆኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ዩክሬን አቅንተው ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬን በተጨማሪ ፖላንድን እና የኔቶ ምስራቅ አውሮፓ እዝንም ጎብኝተዋል።
“ፕሬዝዳንት ፑቲን ጦርነቱን የጀመረው አውሮፓን እና ኔቶን ለመበተን ነበር ነገር ግን እኛ የበለጠ ጠነከርን” ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ዩክሬን ድል ማድረጓ አይቀሬ እንደሆነም አክለዋል።
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ በበኩላቸው የፕሬዝዳንት ባይደን ጉብኝት “ቴአትር” ነው ሲሉ አጣጥለዋል።
የአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ጥረት የዩክሬንን ሽንፈት መሸፋፈን እና ናዚዎችን ከውድቀት መታደግ ነው ያሉት ሚኒስትሩ አሁን ላይ በቅዝቃዜ ምክንያት ጦርነቱ መቆሙን ተናግረዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሀገሪቱ ህግ አውጪ እና ብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ምዕራባዊያን ለዩክሬን እያደረጉት ባለው ገደብ አልባ ድጋፍ ምክንያ ከዚህ በፊት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ማቋረጧን ገልጸዋል።
የሩሲያን አዲስ ውሳኔ ተከትሎም የኑክሌር ጦርነት ሊጀመር ይችላል የሚል ፍርሃት በአውሮፓ አንዣቧል።