ፕሬዝዳንት ባይደን በዋርሳው ከኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ይመክራሉ
ባይደን የሩሲያውን አቻቸው “አምባገነን” ካሉ ከስአታት በኋላ ሩሲያ ከ2010ሩ የኒዩክሌር ስምምነት መውጣቷን መግለጿ ይታወሳል
ፕሬዝዳንቱ የኔቶ የምስራቅ ክንፍ አባል ሀገራት ከሩሲያ ሊደርስባቸው የሚችል ጥቃትን መመከት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነው ምክክር የሚያደርጉት
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በፖላንድ ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከቡካሬስት 9 ቡድን አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ነው የሚወያዩት።
ፖላንድ፣ ቡልጋሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ኢስቶኒያ፣ ሃንጋሪ፣ ላቲቪያ፣ ሮማኒያ እና ስሎቫኪያን ያካተተው ቡድን ሩሲያ በ2014 ክሬሚያን ከያዘች በኋላ የተቋቋመ ነው።
ሞስኮ ከአንድ አመት በፊት በኬቭ ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህም ሀገራቱ ስጋታቸው ከፍ እያለ መምጣቱን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
- የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩክሬን ድንገተኛ ጉብኝት እያደረጉ ነው
- ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመቀነስ ከአሜሪካ ጋር ደርሳ ከነበረው ስምምነት መውጣቷን አስታወቀች
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በዋርሳው ከሀገራቱ መሪዎች ጋር ሲመክሩም፥ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኬቭ ድንገተኛ ጉብኝት አድርገው ከትናንት በስቲያ ፖላንድ የገቡት ባይደን፥ በአደባባይ ፑቲንን “አምባገነን ነው፤ ልንቃወመው ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ ንግግራቸው ከስአታት በኋላም ፕሬዝዳንት ፑቲን በፓርላማ ምዕራባውያኑን የከሰሱበት ዘለግ ያለ ንግግር አድርገዋል።
ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን ጦርነት 150 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን በመጥቀስም ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ናቸው ብለዋል።
ሩሲያ የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ እሽቅድምድምን ለማስቆም በፈረንጆቹ 2010 ከአሜሪካ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት ማቋረጧንም ነው ያነሱት።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅትን ወደምስራቅ የማስፋፋት የዋሽንግተን ፍላጎት ሊገታ አለመቻሉንም በመጥቀስ።
ፕሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ኔቶን የተቀላቀሉ ሀገራት መሪዎችን ለማነጋገር ተዘጋጅተዋል።
አሜሪካ ለሀገራቱ በተለይ የአየር ጥቃት መከላከያ መሳሪያዎችን በሽያጭ እና ድጋፍ በምታቀርብበት ሁኔታ ላይም ይመክራሉ ነው የተባለው።
ዩክሬንን የኔቶ አባል የማድረግ ሙከራ ሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻውን እንድትጀምር ካስገደዷት ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው መሆኑ ተደጋግሞ ተነስቷል።