ጆ ባይደን እና ዢ ጂንፒንግ 'ቀይ መስመር' ስለሆኑ ጉዳዮች ሊወያዩ ነው
የሁለቱ መሪዎች ንግግር የታይዋን ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ባይደን ተናግረዋል
ጆ ባይደን እና ዢ ጂንፒንግ ከሁለት ዓመት ወዲህ በአካል ሲገናኙ የመጀመሪያ ይሆናል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቻይና አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው ቡድን 20 የመሪዎች ጉባኤ ላይ የመገናኘት እቅድ እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
ሁለቱ መሪዎች በብሄራዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል።
የዩኤስ ፕሬዝዳንት በዋይት ሀውስ “ምንም አይነት መሰረታዊ ስምምነት ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለሁም” ሲሉ ከቻይና መሪ ጋር ባደረጓቸው በርካታ ስብሰባዎች ለፕሬዝዳንት ጂንፒንግ“እኔ ፉክክርን እንጂ ግጭትን አልፈልግም" ብያቸዋለሁ ብለዋል።
የቡድን 20 መሪዎች የሁለት ቀን ስብሰባ በፈረንጆቹ ህዳር 15 እና 16 በኢንዶኔዥያ ይካሄዳል።
ዋሽንግተንም ሆኑ ቤጂንግ ለሚጠበቀው ንግግር ትክክለኛ ቀን እና ሰዓት ይፋ አላደረጉም።
ባይደን ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ከሁለት ዓመት በኋላ ሁለቱ ሠሪዎች በአካል ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንት ጅንፒንግ በቻይና ገዥ ኮሙኒስት ፓርቲ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ከተመረጡ ከሳምንታት በኋላ በአንድ ትልቅ የፖለቲካ ዝግጅት ላይ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ይሆናል ተብሏል።
"በምንነጋገርበት ጊዜ ማድረግ የምፈልገው እያንዳንዱ ቀይ መስመሮቻችን ምን እንደሆኑ እንዲገልጹና ከእነዚህም ውስጥ ለቻይና ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅም የትኞቹ እንደሆኑ መጠየቅ ነው" ሲሉ የንግግሩን አቅጣጫ ጠቁመዋል።
ቻይና የግዛቴ አካል የምትላት የታይዋን ጉዳይ የንግግሩ አንዱ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ባይደን መናገራቸውን ኒውስ ዊክ ዘግቧል።
አሜሪካ ከአንድ ቻይና ፖሊሲ በማፈንገጥ ከታይዋን ጋር ግንኙነት ለመመስረት እየጣረች ነው በሚል የቤጂንግና ዋሽንግተን ግንኙነት ከሻከረ ሰንብቷል።
ባይደን ሀገራቸው ይህን ፖሊሲ የመሻር ፍላጎት እንደሌላት ገልጸው፤ ነገር ግን የታይዋንን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደግፋለን ብለዋል።
ቻይና ስለ መሪዎቹ ተጠባባቂ ንግግር በውጭ ጉዳይ ሚንስቴሯ በኩል "ከአሜሪካ ጋር በጋራ ለመስራት ፍቃደኞች ነን" ብላለች።
የጋራ መከባበር፣ ሰላማዊ መኖርና የአሸናፊ ትብብርን እውን ለማድረግ ፍላጎት አለኝ ብላለች። ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ሉዓላዊነትን፣ ደህንነት እና የልማት ጥቅሞቻችንን በቆራጥነት በመጠበቅ ታይዋን ዛሬም “ዋና የፍላጎቴ አካል ነች” ብለዋል።