በሳምንት አምስት ቀናት የአካል ብቃት ማነቃቂያ ህክምና እንደሚወስዱ ተገልጿል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአደባባይ መድረኮች ላይ ላለመውደቅ ልዩ ጫማ ማድረግ ጀመሩ።
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሚገኙባቸው ትላልቅ ሀገራዊ ሁነቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲያደናቅፋቸው እና ሲወድቁ ታይተዋል።
የ81 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ባይደን ይህንን የመደናቀፍ እና መውደቅ ለመከላከል በሚል ልዩ ጫማ እየተጫሙ እንደሆነ ተገልጿል።
አዲሱ ጫማ ተረከዝ አልባ የሆነ ስኒከር ነው የተባለ ሲሆን በተለይም በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጊዜ ለምቾት ተስማሚ ነውም ተብሏል።
እስከ 200 ዶላር ዋጋ ያወጣል የተባለው ይህ የምቾት ጫማ ፕሬዝዳንት ባይደን በተደጋጋሚ ተጫምተውት በአደባባዮች መታየታቸውን ፖለቲኮ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ፕሬዝዳንት ባይደን ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ ሲያደርጉት እንደታዩ ሲገለጽ ከመውደቅ እና መደናቀፍ ታድጓቸዋልም ተብሏል።
የነጩ ቤተ መንግሥት ምክትል ቃል አቀባይ አንድሪው ቤትስ ፕሬዝዳንት ባይደን ከተለመደው የፕሮቶኮል ጫማ ይልቅ ለደህንነታቸው የተሻለውን ስኒከር በመጠቀም ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ እያደረጉት ያለው ይህ ጫማ በተለምዶ አስቸጋሪ መልከዓምድር ወይም ተራራማ ስፍራዎች ላይ የሚደረግ አይነት ጫማ እንደሆነም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ባይደን አካላቸውን የበለጠ ጠንካራ እና ዝግጁ ለማድረግ በሳምንት አምስት ጊዜ የአካል ብቃት ማነቃቂያ ህክምና እያደረጉ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።