ባይደን በኢራቅ የአየር ድብደባ እንዲፈጸም አዘዙ
በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች መቁሰላቸውን ተከትሎ ነው ዋሽንግተን ድብደባውን ያካሄደችው
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በኢራቅና በሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች 100 የሚጠጉ የጥቃት ሙከራ ተደርጎባቸዋል ተብሏል
አሜሪካ በኢራቅ ሶስት የአየር ጥቃቶችን መፈጸሟን አስታወቀች።
በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ የተፈጸሙት ጥቃቶች ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን ላቆሰለው የድሮን ጥቃት የአጻፋ እርምጃ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ልሊዩድ ኦስቲን ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በኢራን በሚደገፉት የካታይብ ሄዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላት ላይ ያነጣጠሩት ድብደባዎች ያደረሱትን ጉዳት በዝርዝር አላብራሩም።
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ በበኩሉ በድሮን የተፈጸሙት ድብደባዎች የካታይብ ሄዝቦላህ ይዞታዎችን ማፈራረሳቸውንና በርካታ የቡድኑ ታጣቂዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ገልጿል።
በቡድኑ ላይ ብቻ ያነጣጠሩት ጥቃቶች በንጹሃን ኢራቃውያን ላይ ጉዳት እንዳላደረሱም ነው ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
ካታይብ ሄዝቦላህ በትናንትናው እለት በኤርቢል ወታደራዊ ጣቢያ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች ለቆሰሉበት የድሮን ጥቃት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ መግለጹን የአሜሪካ የደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ አንድሪ ዋትሰን ገልጸዋል።
አሜሪካ በኢራቅና ሶሪያ የአይኤስአይኤስ የሽብር ቡድንን ለመዋጋት የገቡ ከ3 ሺህ 400 በላይ ወታደሮች አሏት።
በኢራን ድጋፍ የሚደረግላቸው ታጣቂዎች በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕረስ፥ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ጥቃቱ መባባሱን ዘግቧል።
የጋዛ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በኢራቅና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች 100 የሚጠጉ የድሮንና ሮኬት ጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸውንም በማከል።
አብዛኞቹ ሙከራዎች ማክሸፉንና ከባድ ጉዳት አለማድረሳቸውን ያስታወቀው የአሜሪካ ጦር፥ በወታደሮች ላይ የመቁሰል አደጋ ያስከተሉ ጥቃቶች መድረሳቸውን ግን ገልጿል።
ዋሽንግተን በህዳር ወርም በካታይብ ሄዝቦላህና ሌሎች በኢራን በሚደገፉ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ድብደባ መፈጸሟ የሚታወስ ነው።
ቴህራን የምታስታጥቃቸው ቡድኖች አሜሪካ በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጭፍጨፋ መደገፍ ካላቆመች በወታደራዊ ጣቢያዎቿ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንደሚገፉበት በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።