ጆ ባይደን በዕድሜ ትልቁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚሳተፉ የቅርብ ረዳቶቻቸው ገለጹ፡፡
የአሁኑ ፕሬዝዳንት በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ የጆ ባይደን የቅርብ ረዳቶች ድጋፍ ለሚያደርጉ ድርጅቶች ገልጸውላቸዋል ተብሏል፡፡ ዴሞክራቶቹ አሁን ላይ የ79 ዓመቱ ፕሬዝዳንት በድጋሚ ላይወዳደሩ ይችላሉ የሚል ፍርሃት ውስጥ ገብተው እንደነበር ተገልጿል፡፡
የጆ ባይደን ወዳጅና የቀድሞ ሴናተር ክሪስ ዶድ ፕሬዝዳንቱ በአውሮፓውያኑ 2024 በሚደረገው ምርጫ እንደሚወዳደሩ እንደነገሯው ገልጸዋል፡፡ የቀድሞው ሴናተር፤ ጓደኛቸውና ፕሬዝዳንታቸው በቀጣዩ ምርጫ በመወዳደራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ጆ ባይደን ከዕድሜ መግፋት እንዲሁም ተቀባይነት ከማጣት አንጻር ላይወዳደሩ እንደሚችሉ ግምቶች ተቀምጠው ነበር ተብሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም የምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ እና ሌሎች ተወዳዳሪ ፖለቲከኞች ወደ ፕሬዝዳንትነት እንዳይመጡ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡
በበይነ መረብ በተካሄደ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ ጆ ባይደን ለሁለተኛ ጊዜ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ገልጸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የነበሩት የፔንሲልቫኒያ ገዥ ፕሬዝዳንት ባይደን በአደባባይ የተናገሩት የሚያምኑበትን እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ስራውን በአካልም ሆነ በስነልቦና ረገድ እንደማይሰሩ ካመኑ ላይወዳደሩ እንደሚችሉም ነው ገዥው የገለጹት፡፡
የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩው ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር፡፡ ጆ ባይደን፤ ዶናልድ ትራምፕን በማሸነፍ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡ ሲሆን በወቅቱ 273 ኤሌክቶራል ድምጽ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
በአሜሪካ በትንሽ ዕድሜያቸው ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆን ኦፍ ኬንዲ ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ የፈጸሙት በ 43 ዓመታቸው ነው፡፡ ጆ ባይደን ደግሞ በ 78 ዓመታቸው ፕሬዝዳንት በመሆን በዕድሜ ትልቁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡