በትግራይ ክልል የተቋረጡ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን በአፋጣኝ መልሶ ማስጀመር ለዘለቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን አሜሪካ ገለፀች
እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በአፋርና በሌሎችም አካባቢዎች ለሚገኙ ማህበረሰቦች ያለ ቅድመ ሁኔታ ሰብአዊ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ የህወሓት ኃይሎች ከቀሪ የአፋር ክልል አካባዎች ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል
በትግራይ ክልል አፋጣኝ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ መጀመር ለዘለቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ይህን ያሉት በትናንትነው እለት እርዳታ የጫኑ 50 ተሸከርካሪዎች ወደ መቀሌ መግባታቸውን ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ነው።
አንቶኒ ብሊንከን፤ ተጨማሪ የነፍስ አድን ሰብአዊ ርዳታ ወደ ትግራይ ክልል መድረሱን አሜሪካ በበጎ የምትመለከተው እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት፣ ትግራይ ክልልን በማስተዳደርው የህወሓት አመራሮች፣ የአፋር ክል ባለስልጣናት እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ግብረሰናይ ድርጅቶች ለተቸገሩ ሁሉ እርዳታ ለመስጠት የሚያደርጉትን ጥረት አሜሪካ እንደምታደንቅም ገልጸዋል።
ብሊንክን “የማያቋርጥ የሰብአዊ አቅርቦት እና አፋጣኝ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ መጀመር ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው”ሲሉም አክለዋል።
ብሊንከን፤ እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በአፋር ክልል የሚኖሩ ህዝቦችን ጨምሮ በስቃይ ላይ ለሚገኙ ማህበረሰቦች ቀጣይነት ያለው፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ እና ያልተደናቀፈ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቿል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት አመራሮች ግጭት እንዲቆም ያሳዩት ቁርጠኝነት ለቀጣይ እርቅ እና ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ብሊንከን፤ የህወሓት ኃይሎች ከአፋር ክልል ከኢሬብቲ ለቆ መውጣቱ በደስታ የምንቀበለው ነው ሲሉም ግልጿል።
በቀጣይም የህወሓት ኃይሎች ከያዟቸው ከአፋር ክልል አካባቢዎች የመውጣቱ ጉዳይ አስፋለጊ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በድርድርና በዘላቂነት ግጭቶችን ለማስወገድ ሁሉም ወገኖች የጀመሩትን እርምጃ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ሂደቶችን ለማሳለጥ በትግራይ ክልል አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ብልጽግናና ደህንነት ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት አስፈላጊና መሰረታዊ ነው” ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ፤ ብትግራይ ክልል እንደ ቴሌኮም፣ ባንክ፣ መብራትና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ከተቋረጡ ከ500 ቀናት በላይ መቆጠራቸው የተመድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በትናንትናው ዕለት አስፈላጊ የሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቶችን የጫኑት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሸከርካሪዎች መቀሌ መድረሳቸው ይታወቃል።
ተሽከርካሪዎቹ 1 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እና ጥራጥሬ፣ 700 ሜትሪክ ቶን የጤና፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የማጠቢያ (ውሃ፣ የአካባቢ እና የግል ንፅህና መጠበቂያ እቃዎች) እንዲሁም 115 ሺህ ሊትር ነዳጅ የጫኑ እንደሆኑም ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም መቀሌ የደረሰውን እርዳታ በዚህ ሳምንት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ማከፋፈል እንደሚጀምር አሳውቋል።
በዚህም ድርጅቱ 43 ሺህ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች እንዲሁም ተጋላጭ ለሆኑ 24 ሺህ እናቶች እና ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ ለመድረስ ማቀዱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ገዜያዊ የጭት ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 20 የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ወደ መቀሌ መግባታቸው የሚታወስ ነው።
ተኩስ መቆሙን ተከትሎ በየቀኑ እርዳታ የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዲገቡ ስምምነት ላይ ቢደረስም ፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታት እርዳታ ሳይገባ መቆየቱ ይታወቃል።
እስካሁን በትንሹ 2 ሺህ ገደማ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ትግራይ ክልል ሊደርሱ ይችሉ እንደነበር ቢገመትም፤ የትናንቱን ጨምሮ 70 የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ብቻ መግባታቸውም ነው የተመድ መረጃ የሚያመለክተው።