ጆ-ባይደን የአሜሪካ ዋና አጋር ወደሆነችው እስራኤል በነገው እለት ያቀናሉ
ባይደን በአስራኤል ቆይታቸው በአንኳር ቀጠናዊ እና ሁለትሽ ጉዳዮች ዙርያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ጋር ይመክራሉ ተብለዋል
“የቴህራን ኒውክሌር የማበልጸግ ጉዳይ” የፕሬዝዳንቱ የቀጣናው ጉብኝት ትኩረት እንደሚሆን ከወዲሁ ተጠብቋል
ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን በነገው እለት የአሜሪካ ዋና አጋር ወደሆነችው ሀገረ እስራኤል የሚያደርጉት ጉዞ በወሳኝ ቀጠናዊና ሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዳዮች የሚመከሩበት ጉብኝት እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡
የቀጠናው ስጋት እንደሆነ የሚነገርለት የቴህራን የኒውክሌር ማበልጸግ ጉዳይ፣ መቋጫ ያልተበጀለት የፍልስጤም ጉዳይ እንዲሁም በባህሬን እና እስራኤል መካከል የተፈረመውና የአብርሃም ስምምነት (ኢብራሂም አኮርድ) ተብሎ በሚታወቀው የሰላም ስምምነት ውስጥ ሌሎች የዓረቡ ዓለም ሀገራት እንዲካተቱበት የማድረግ ጉዳይ ጆ-ባይደን በጉብኝታቸው ከአስራኤል መሪዎች ጋር የሚመክሩባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ናቸው፡፡
እስራኤላውያን ከቪዛ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚችሉበት አሰራር እንዲኖር ማድረግ እና አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል የምትችልበት ሂደት ማጽናት የሚሉት ደግሞ ፕሬዝዳንት ባይደን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ ጋር የሚወያዩባቸው አንኳር የሁለትዮሽ አጀንዳዎች ናቸው ተብለው ይጠበቃሉ፡፡
የቀድሞው የእስራኤል ጦር የስለላ ክፍል ሃላፊ ታሚር ሀይማን እና የእስራኤል ወታደራዊ ኢንተለጀንስ የጥናት ክፍል ኃላፊ ከነበሩት ከኤልዳድ ሻቪት ጉብኝቱን በማስመልከት ባደረጉት ጥናትና በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ጥናት ተቋም አማካኝነት ባወጡት ጥናታዊ ጽሁፋቸው “የቴህራን የኑክሌር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ስምምነቱ አሁንም ግልጽ አይደለም፤ የኒውክሌር ማበልጸግ መርሃ ግብሯ አሁንም እንደቀጠለችበት ነው፤ እናም ኢራን የፕሬዝዳንቱ የቀጣናው ጉብኝት ትኩረት ትሆናለች” ብለዋል፡፡
“በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል የቅርብ ቅንጅት አስፈላጊ ነው፣ እናም እስራኤል በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚው ረገድ ቀይ መስመሮች ናቸውም የምትላቸው ጉዳዮች በግልጽ በማስቀመጥ የአሜሪካን ድጋፍ ቀጣይነት ማረጋገጥ አለባት" ይህ ማለት ደግሞ በሶሪያ ውስጥ ያሉ የኢራን እና የሂዝቦላ ዒላማዎችን መምታት እንደማለት ነው ሲሉም አክለዋል የኢንተለጀንስ ባለሙያዎቹ፡፡
የቀድሞ የእስራኤል ወታደራዊ እንተለጀንስ ባልደረቦቹ ታሚር ሀይማን እና ኤልዳድ ሻቪት፤ ባይደን እስራኤልን ለመጎብኘት መወሰናቸው በግለሰብ ደረጃም ጭምር ከአስራኤል ጋር ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት የተንጸባረቀበት እንደሆነም በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡
የፕሬዝዳንት ባይደን የእስራኤል ጉብኝት ለቀጣናው መግባባት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ያሉት ሀይማን እና ሻቪት፤ እስራኤል ለአሜሪካ ያላትን ዘላቂ አጋርነት የምታረጋግጥበት ምእራፍ አሁን መሆኑም ጠቁመዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን በእስራኤል የሚኖራቸውን ቆይታ ሲያገባድዱ ከሳዑዲ አረቢያ እና በባህረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት ከሚገኙ የግብጽ፣ ኢራቅ እና ዮርዳኖስ መሪዎች ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብለዋል፡፡