"ፑቲን የአውሮፓን ፊንላንድነት ቢፈልግም፤ በቅርቡ ኔቶ ሆኖ ያገኘዋል" - ባይደን
በፖላንድ ቋሚ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንደሚቋቋምም ነው ባይደን የተናገሩት
ፕሬዝዳንት ባደን አሜሪካ፤ በአውሮፓ ያላትን ወታደራዊ ይዞታ እንደምታጠናክር ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሃገራቸው በአውሮፓ ያላትን ወታደራዊ ይዞታ እንደምታጠናክር ተናገሩ፡፡
ባይደን ይህን የተናገሩት በስፔን ማድሪድ በመካሄድ ላይ ባለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሃገራት ስብሰባ ላይ ነው፡፡
በስብሰባው በመሳተፍ ላይ ያሉት ባይደን የኔቶ አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን እንደሆነ ለማረጋገጥ ይበልጥ እናጠናክረዋለን ብለዋል፡፡
በፖላንድ ቋሚ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እንደሚቋቋምም ነው ባይደን የተናገሩት፡፡
በሩማኒያ ተጨማሪ 3 ሺ ወታደሮችን ለማስተናገደፍ የሚችል ተዘዋዋሪ ብርጌድ እንደሚኖር፣ በባልቲክ አካባቢ ያለው ወታደራዊ ስምሪት እንደሚሻሻልም ጠቁመዋል፡፡
ተጨማሪ ሁለት የአሜሪካ ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶች በብሪታኒያ እንደሚሰማሩ የተናገሩም ሲሆን ጣቢያ በጀርመን እና በጣሊያን ተጨማሪ የአየር እና ሌሎች የመከላከያ መንገዶች እንደሚጠናከሩም ገልጸዋል፡፡
"ከወዳጆቻችን ጋር በመሆን ኔቶ በየትኛውም አቅጣጫ በየትኛውም መንገድ ላሉ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት የሚችል እንዲሆን እናደርገዋልን " ሲሉም ተናግረዋል ባይደን፡፡
ኔቶ ስበሰባውን በማካሄድ ላይ ያለው ቱርክ ይዛው በነበረው አቋም ጉዳይ ያስመዘገባቸውን ዲፕሎማሲያዊ ድሎች በማጣጣም ነው፡፡
ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን መቀላቀል የለባቸውም ከሆነም ዋስትና ሊሰጠኝ ይገባል በሚል የሃገራቱን መቀላቀል ተቃውማ የነበረችው ቱርክ አሁን ተቋውሞዋን አንስታለች፡፡
ይህ ዩክሬን ኔቶን እንዳትቀላቀል በማሰብ ጦርነት ለጀመሩት ቭላድሚር ፑቲን ትልቅ ዲፕሎማሲዊ ኪሳራ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ፑቲን በስተ ምስራቅ በኩል ረጅም ድንበርን ከሃገራቸው ጋር የምትዋሰነው ፊንላንድም ሆነች ስዊድን አሜሪካ መራሹን ጥምረት እንዲቀላቀሉ አይፈልጉም ነበር፡፡ ሆኖም ኔቶ ይበልጥ ለሩሲያ የሚቀርብበት ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡
ሁኔታውን አስመልክተው የተናገሩት ባይደን "ፑቲን የአውሮፓን ፊንላንድነት (ፊንላንዳይዜሽን) ነበር የሚፈልገው፤ አሁን ግን አውሮፓ ኔቶ ሆኖ (ኔቶናይዜሽን) ሊያገኘው ነው፤ በእርግጥ ይህን አይፈልገውም እኛ ግን ለአውሮፓ ደህንነትን ሲባል መሆን እንዳለበት እናምናለን" ብለዋል።
ይህን ቀደም ሲልም የተቃወመችው ሩሲያ ኔቶ ወደ ክሬሚያ የሚጠጋ ከሆነ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ ማለት ነው ስትል ማስጠንቀቋ የሚታወስ ነው፡፡