ትራምፕና ፔንስን በማሸነፍ የአሜሪካ መሪነትን ማሸነፋቸው በመጽሔቱ ለመመረጣቸው ምክንያት ነው
ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ለመግባት 40 ቀናት የቀራቸው ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንና ምክትላቸው ካማላ ሃሪስ የታይም መጽሔት የዓመቱ ሰዎች በሚል ተመርጠዋል፡፡
ታይም መጽሔት ሁለቱንም ፖለቲከኞች የዓመቱ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በሚል የመረጠው ተሰናባቹን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን በምርጫ በማሸነፋቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን ተመራጯ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የመጀመሪያዋ ሴት፣ የመጀመሪያዋ የጥቁር እና የደቡብ እስያ ዝርያ ያላቸው ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የመረጣቸው ጆ ባይደን በሀገሪቱ ታሪክ በእድሜ ትልቁ ፕሬዝዳንት በመሆንም ክብረወሰን ይይዛሉ፡፡
አሜሪካ በከፍተኛ መከፋፈል ውስጥ ሆና ባካሔደችው በዘንድሮው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ባልተጠበቀ መጠን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ድምጹን ሰጥቷል፡፡
ምንም እንኳን ዶናልድ ትራምፕ መሸነፋቸውን እስካሁን በይፋ ባይገልጹም ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በመሆን ማሸነፋቸው ግን ይፋ ተደርጓል፡፡
ከባይደንና ሃሪስ በተጨማሪም የዙም መተግበሪያ መስራች ኤሪክ ዩዋንም የዓመቱ ምርጥ የቢዝነስ ሰው ተብሎ ተመርጧል፡፡
ታይም መጽሔት ከአውሮፓውያኑ 1927 ጀምሮ የተመረጡ ምርጦች በሚል ስያሜ ምርጥ ያላቸውን ሲሰይም ቆይቷል፡፡ በ2006 ደግሞ የዓመቱ ሰው መባል መጀመሩ ይታወሳል፡፡