ወሳኝ የአሜሪካ ተቋማት የጆ ባደንን ምርጫ ድል መቀበል መጀመራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ
ወሳኝ የአሜሪካ ተቋማት የጆ ባደንን ምርጫ ድል መቀበል መጀመራቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባደን ምርጫውን ቢያሸንፉም ተሰናባቹ ፕሬዚዳት ዶናልድ ትራምፕ አልቀበልም ብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ አንዳንድ የአሜሪካ ተቋማት የምርጫውን ውጤት መቀበል መጀመራቸውን የሚያስችል ሥራዎችን እያከናወኑ ነው ተብሏል፡፡ ለአብነትም የአሜሪካ ጠቅላላ አገልግሎት አስተዳደር የተሰናባቹን እና የተመራጩን ፕሬዚዳንቶች የሽግግር ሂደት እንዲጀመር የሚያዝ ይፋዊ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
የአሜሪካ ጠቅላላ አገልግሎት አስተዳደር ኃላፊ ኢሚሊ መርፊ በጻፉት ደብዳቤ ባይደን ይህ የሽግግር ሂደቱን መጀመር እንደሚችሉና የሚያስፈልጋቸው ድጋፍም እንደሚደረግላቸው በደብዳቤ ገልጸዋል፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ማሸነፋቸውን ከሁለት ሳምንት በፊት ቢገልጹም ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ይህንን ሳይቀበሉ ቆይተዋል፡፡
ኃላፊዋ ይህ የሽግግር ሂደት እንዲዘገይ ከማንም ጫና እንዳልደረሰባቸው የገለጹ ሲሆን እርሳቸው ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ስራቸውን መስራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ አንዳንድ የሕግ ጉዳዮች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡
ይህ የሽግግር ሂደት እንዲጀመር የወሰንኩት በነጻነትና በሕግ መሰረት እንደሆነ ሁሉም ማወቅ አለበት ያሉት ኃላፊዋ ውሳኔው የተወሰነው መሬት ላይ ያሉ ዕውነታዎችን በመረዳት የተደረገ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡የሀገሪቱ ጠቅላላ አገልግሎት አስተዳደር የጻፈው ደብዳቤ የሽግግር ሂደቱ በይፋ እንዲጀመር ከማመላከቱም በላይ ዶናልድ ትራምፕ ሽንፈታቸውን ማመናቸውን ያመለክታል ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን በይፋ ደብዳቤው አሁን ቢገለጽም ተመራጩ ፕሬዚዳንት ግን ሂደቱን ጀምረው እንደነበር ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ጆ ባይደን አንቶኒ ብሊንከንን ነው ቀጣዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ጃክ ሱሊቫንን ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ፣ ሊነዳ ቶማስን ግሪን ፊልድን ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አድርገው እንደሚሾሙ ገልጸዋል፡፡