የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሆሊውድን ሊቀላቀሉ ነው?
ባይደን ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናዮችን ከሚያገለግለው ሲኤኤ ከተሰኘው ተቋም ጋር ውል ተፈራርመዋል
የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በባይደን ውሳኔ መገረማቸውን ተናግረዋል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሆሊውድን ሊቀላቀሉ ነው?
ላለፉት አራት ዓመታት የአሜሪካ 46ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ጆ ባይደን መሰረቱን ሆሊውድ ካደረገው የኪነ ጥበብ ተቋም ጋር ተፈራርመዋል፡፡
በምህጻረ ቃሉ ሲኤኤ በሚል የሚታወቀው ኩባንያ ዝነኛ የሆሊውድ ተዋናዮችን የኪነ ጥበብ ስራዎች፣ ንብረቶች፣ የምስል መብት እና ሌሎች አገለግሎቶችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
ከ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ እና የምርጫ ዘመቻ ከጀመሩ በኋላ ራሳቸውን ያገለሉት ጆ ባይደን ከዚህ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ፎክስ ኒውስ ጆ ባይደን ከሲኤኤ ኩባንያ ጋር መፈራረማቸውን አስመልክቶ ምን አስተያየት እንዳላቸው ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን ምላሻቸውም ፈገግ አሰኝቷል፡፡
የእውነት ባይደን ተፈራረመ? ሲሉ መልሰው የጠየቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በውሳኔው መገረማቸውን ተናግረዋል፡፡
“እኛ እሱ የፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየታገልን ነው፣ እሱ ግን ቀሪ ህይወቱን ዘና ለማለት ከሲኤኤ ጋር ተፈራረመ“ ሲሉም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሲኤኤ ኩባንያ በበኩሉ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደንበኛው እንደሆኑ ገልጾ በአሜሪካ እና በመላው ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው የተሸለ ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ይደግፋሉ ብሏል፡፡
ጆ ባይደን ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት በካንሰር ህመም ህይወቱ ባለፈው ልጃቸው ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ “ቃል ግባልኝ አባቴ” የተሰኘ መጽሀፍ አላቸው፡፡
የጆ ባይደን እና ሲኤኤ ስምምነት ግልጽ ባይሆንም ከዚህ መጽሀፋቻው ጋር በተያያዘ ስራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ እና የኪነ ጥበብ ውጤቶችን ለማስተዳደር ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡
ሲኤኤ ከጆ ባይደን ባለፈ ባራክ ኦባማ እና ባለቤታቸው ሚሼል ደንበኞቹ እንደሆኑም አስታውቋል፡፡