የምርጫውን አሸናፊ ለማወቅ የአራት ግዛቶች ውጤት ይጠበቃል
የምርጫውን አሸናፊ ለማወቅ የአራት ግዛቶች ውጤት ይጠበቃል
ምንም እንኳን በትራምፕ እና ባይደን መካከል ለኋይት ሀውስ የሚደረገው ፍልሚያ ቢቀጥልም ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል እስካሁን ቁርጥ ያለ ምላሽ የለም፡፡
አሸናፊው ሳይታወቅ ቀናት ሊቆጠሩ እንደሚችሉም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከኮሮና ቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ በፖስታ የተሰጡ በርካታ ድምጾችን ለመቁጠር ጊዜ ይወስዳል መባሉ ነው፡፡ እንደ ሚቺጋን፣ ዊስኮንሲን እና ፔንሲልቫንያ ያሉ ከፍተኛ ድምጽ ያላቸው ግዛቶች ገና ቆጠራ ያልተጠናቀቀባቸው ናቸው፡፡
የምርጫው ውጤት ሊቆይ የሚችልበት ሌላኛው ምክንያት በሂደቱ የህግ አካላት ሊሳተፉ የሚችሉበት ዕድል በመኖሩ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሊያመሩ እንደሚችሉ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሂደቱ ሳምንታትን ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል፡፡
ሌላው ቢቢሲ እንደምክንያት ያስቀመጠው መጠራጠሮች አለመረጋጋት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በብዙ አሜሪካዊያን ዘንድ ስጋት ቢፈጥርም አሁን ላይ አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል ለማለት ብዙም የሚያስደፍር ነገር የለም የሚሉ አካላትም አሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትራምፕ ምርጫውን በርግጠኝነት አሸንፊያለሁ ማለታቸው ከዴሞክራት ፖለቲከኞች ከፍተኛ ትችት እያስከተለባቸው ነው፡፡
የባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድንም ትራምፕ ወደ ፍርድ ቤት ለክስ ካመሩ ለመከላከል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ትራምፕ ዋና ዋና በሚባሉ ግዛቶች በጠባብ ልዩነት በመምራት ላይ የሚገኙ ሲሆን ድምጽ የመስጠት ሂደቱ የተያዘለት ጊዜ ካበቃ በኋላ ቀጥሏል የሚል ተቃውሞ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡
እስካሁን ተቆጥረው ባለቁ ውጤቶች መሰረት ባይደን 238 ወካይ ድምጽ በማግኘት እየመሩ ሲሆን ትራምፕ በ213 ድምጽ ይከተላሉ፡፡
ፕሬዝዳንት በመሆን ኋይት ሀውስ ለመግባት ከአጠቃላዩ 538 ወካይ ድምጽ ከሁለት አንዳቸው 270 ድምጽ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከአራት ቁልፍ ግዛቶች የሚገኘው ውጤት በምርጫው ማን እንደሚያሸንፍ የሚወስን ሲሆን ግዛቶቹ ፔንሲልቬንያ ፣ ሚሺጋን ፣ ጆርጂያ እና ዊስኮንሲን ናቸው፡፡