ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት የትራምፕ ቡድን ከወዲሁ ክስ መስርቷል
ተቆጥረው ያላለቁ ጥቂት ድምጾች ቀጣዩን ፕሬዝዳንት ይወስናሉ
የመጨረሻው ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት ሁለቱ ተፋላሚዎች ፣ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ፣ ስለማሸነፍ ተናግረዋል፡፡
የዴሞክራቱ እጩ ባይደን ረቡዕ ምሽት ላይ ባደረጉት ንግግር እርሳቸው እና ካማላ ሀሪስ እንደሚያሸንፉ በመተማመን የአሜሪካ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት በመስጠት ከፍተኛ የመራጮችን ተሳትፎ አድንቀዋል፡፡
ጆ ባይደን ለደጋፊዎቻቸው ባደርጉት ንግግር "ወደ ድል እየተቃረብን እንደሆነ እናምናለን" ብለዋል።
16 ድምጽ ባለው ሚቺጋን ማሸነፋቸውን ያረጋገጡት ባይደን በእስካሁኑ ውጤት እውነትም ወደ ድል የተቃረቡ ይመስላሉ።
ልብ አንጠልጣይ እንደሆነ በቀጠለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት እስካሁን 264 ወካይ ድምጽ ማግኘታቸውን ያረጋገጡት ባይደን ድላቸውን ለማረጋገጥ 6 ድምጽ ብቻ ይቀራቸዋል። አብዛኛው ቆጠራ ተከናውኖ በ0.6 በመቶ ጠባብ ልዩነት በሚመሩት ኔቫዳ ካሸነፋ ኋይት ሀውስ ለመግባት የሚያስችላቸውን ዝቅተኛውን 270 ወካይ ድምጽ ማሳካት ይችላሉ።
ውጤታቸው ባልታወቀ በተቀሩት 4 ግዛቶች ትራምፕ እየመሩ ሲሆን ኔቫዳን ጨምሮ በነዚህ ግዛቶች ካሸነፉ ለሁለተኛ ጊዜ በመሪነት ይቀጥላሉ።
ቀጣዩን ፕሬዝዳንት የሚወስኑት ግን ተቆጥረው ያላለቁ ጥቂት ድምጾች ናቸው፡፡
በአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ታሪክ በከፍተኛ ህዝብ በመመረጥ መሪነቱን የያዙት ባይደን "እዚህ የተገኘሁት ማሸነፋችንን ለማወጅ ሳይሆን ቆጠራው ሲጠናቀቅ እንደምናሸንፍ ያለኝን እምነት ለመግለጽ ነው" ብለዋል።
"ምርጫው ተጭበርብሯል" በማለት ትራምፕ ክስ መክፈታቸውን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር "ስልጣን አንስተው የሚወስዱት ሳይሆን ከህዝብ የሚገኝ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
በንግግራቸው ማጠቃለያም የሁለቱም ደጋፊዎች እርስ በእርስ በጠላትነት እንዳይተያዩ ጠይቀዋል ሲል ዘ ናሺናል ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ክስ መክፈታቸው ተዘግቧል።
የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ማለዳ ላይ ከቡተ-መንግሥት ባደረጉት ንግግር "ዴሞክራቶች ምርጫውን በማጭበርበር ለመስረቅ እየሞከሩ ነው" በማለት ማስረጃ የሌለው ከስ ሰንዝረዋል፡፡
የምርጫው ውጤት ገና ሳይታወቅ ስለማሸነፋቸው የተናገሩት ትራምፕ ከተሸነፉ ለክስ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩም ገልጸው ነበር፡፡
የትራምፕ ቡድን ፕሬዝዳንቱ በሚመሩባቸው ግዛቶች ቆጠራው እንዲያበቃ እና በተሸነፉበት ዊስኮንሲን ደግሞ የድምጽ ቆጠራው እንደ አዲስ እንዲካሔድ በመጠየቅ ከወዲሁ ክስ መስርቷል፡፡ በቆጠራው ሂደት ግልጽነት ይጎለዋል በሚል ነው የፕሬዝዳንቱ የምጫ ዘመቻ ቡድን ክስ የመሰረተው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቂት የትራምፕ ደጋፊዎች ቆጠራው እንዲቋረጥ በሚል በዴትሮይት ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የጆ ባይደን ደጋፊዎች ደግሞ ሁሉም ድምጽ ይቆጠር የሚል ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል፡፡
በጉጉት እየተጠበቀ ያለው የሀገሪቱ ምርጫ ውጤት ከወዲሁ ውጥረት በመፍጠር ላይ ስለመሆኑ ሁኔታዎች በማመልከት ላይ ናቸው፡፡