ውጤቱን ዓለም በጉጉት ይጠብቀዋል
ልብ አንጠልጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት እስካሁን ይፋ አልሆነም
ሀገሪቱ ካላት ተጽዕኖ አንጻት አሜሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም በጉጉት የሚጠባበቀው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በከፍተኛ ፉክክር ቀጥሏል፡፡
እስከ ቅርብ ደቂቃዎች ድረሰስ የምርጫውን ውጤት ይወስናሉ በሚባሉት ግዛቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲመሩ የቆዩ ሲሆን አሁን ላይ ሁለት ግዛቶች ወደ ዴሞክራቶቹ ጆ ባይደን ማጋደል ጀምረዋል፡፡
በተለይ በፖስታ የተሰጠው ድምጽ ቆጠራ ዘግይቶ የተጀመረ ሲሆን በዚህ መልኩ የተሰጠው ድምጽ ባይደን እንዲያንሰራሩ አድርገዋቸዋል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉት ግዛቶች አሁን ላይ ትራምፕ በጆርጂያ እና በሰሜን ካሮላይና በጠባብ ልዩነት በፔንሲልቫኒያ ደግሞ ሰፋ ባለ ልዩነት እየመሩ ነው፡፡
ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን ደግሞ በሚሺጋን ኔቫዳ እና ዊስኮንሲን በጠባብ ልዩነት ይመራሉ፡፡
ውጤቱ ባልተገለጸባቸው 9 ግዛቶች አብዛኛው ድምጽ ተቆጥሮ አልቋል፡፡ እስካሁን በተጠናቀቁ ሪፖርቶች ባይደን 238 ወካይ ድምጽ በማግኘት በመምራት ላይ ሲሆኑ ትራምፕ 213 ድምጾችን አግኝተዋል፡፡ ለማሸነፍ 270 ድምጽ ማግኘት የሚያስፈልግ ሲሆን የተቀሩት ግዛቶች ውጤት ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡