ምርጫውን ካላሸነፉ ለክስ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንደሚሔዱ ትራምፕ ተናገሩ
እስካሁን በተቆጠሩ ድምጾች ባይደን በመምራት ላይ ሲሆኑ ትራምፕ ድምጽ እየተሰረቀ ነው ብለዋል
የምርጫው ሙሉ ውጤት ይፋ ከመደረጉ በፊት ትራምፕና ባይደን ማሸነፋቸውን እየገለጹ ነው
የምርጫው ሙሉ ውጤት ይፋ ከመደረጉ በፊት ትራምፕና ባይደን ማሸነፋቸውን እየገለጹ ነው
የምርጫው ሙሉ ውጤት ይፋ ባይደረግም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርጫውን ማሸነፋቸውን በኋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡
“በርግጠኝነት ምርጫውን አሸንፈናል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ በምርጫው “የመረጡኝን ሁሉ አመሰግናለሁ ፤ እናም ድላችንን ለማክበር ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡
ይሁንና ምርጫው እየተጭበረበረ ነው ያሉት ትራምፕ ያለምንም ማስረጃ ድምጽ የመስረቅ ተግባር በመከናወን ላይ ነው ብለዋል፡፡
“ይህ ለአገራችን አሳፋሪ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ በምርጫው የሚሸነፉ ከሆነ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለመሄድ ማቀዳቸውንም አክለዋል፡፡
ትዊተር እና ፌስቡክ ትራምፕ ማሸነፋቸውን በመግለጽ ድምጽ እየተሰረቀ ነው በሚል የለጠፉትን ጽሁፍ መደበቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ትዊተር ፕሬዝዳንቱ የለጸጠፉትን ጽሁፍ ስለምርጫው የተሳሳተ መረጃ የሚሰጥ ነው ብሏል፡፡
ሚስተር ትራምፕ ከምርጫው ቀን አንድ ሳምንት ቀደም ብለው የእርሳቸው ደጋፊ የሆኑትን ዳኛ ኤሚ ኮኒ ባሬትን ከአሜሪካ ጠቅላይ ፍ / ቤት ዳኞች አንዷ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ይህም ባልተለመደ መልኩ በፍርድ ቤቱ የሪፓብሊካኑ ደጋፊ ዳኞች እንዲበልጥ አድርጓል፡፡
ጆ ባይደን ደግሞ በዴላዋሬ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር በማሸነፍ ጉዞ ላይ እንደሆንን እናምናለን ብለዋል፡፡
ይሁንና የመጨረሻው ውጤት ይፋ እስኪደረግ በትዕግስት መጠበቅ አለብን ነው ያሉት የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት በንግግራቸው፡፡ ሁሉም ድምጽ ተቆጥሮ እስኪያልቅ ምርጫው ተፈጽሟል ማለት አይቻልም ያሉት ባይደን ነገር ግን እስካሁን ያለን ውጤት አስደሳች ነው ብለዋል፡፡
ታይም ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ተቖጥረው ባለቁ ውጤቶች መሰረት ባይደን 238 ወካይ ድምጽ በማግኘት እየመሩ ሲሆን ትራምፕ በ213 ድምጽ ይከተላሉ፡፡ ይሁንና በመጨረሻው ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚኖራቸው የተወሰኑ ግዛቶች ውጤት ገና ይጠበቃል፡፡
ፕሬዝዳንት በመሆን ኋይት ሀውስ ለመግባት በትንሹ ከአጠቃላዩ 538 ወካይ ድምጽ 270 ድምጽ ማግኘት ይጠበቃል፡፡