መንግስት፤ ተማሪዎች እና ማህበረሰቡ "ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ተላላኪዎች" ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳሰበ
ማሳሰቢያውን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ግብረ ኃይሉ አስታውቋል
ህግ የማስከበር ስራ እየተሰራ ባለበት በዚህ ወቅት "አንድ መሆን እንጂ ውዥንብር ውስጥ ገብቶ መከፋፈል አይጠበቅብንም" ብሏል
መንግስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ማህበረሰቡ የተከሰተውን ችግር ምክንያት በማድረግ ሆን ብለው ግጭት ለማነሳሳት እየተደረጉ ካሉ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳሰበ፡፡
የኢፌዴሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከሰሞነኛ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዘ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በቅርቡ በጋምቤላ ከተማና አካባቢው እንዲሁም በጊምቢና ደምቢ ዶሎ ከተማ የጥቃት ሙከራ መደረጉን ያስታወሰው ግብረ ኃይሉ ሙከራ አድራጊዎቹ ቡድኖች "በከፍተኛ ደረጃ ተደምስሰው ተፈጥሮ የነበረውም ችግር ተወግዶ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ" እንዲመለስ ተደርጓል ብሏል።
ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኖቹ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊንቢ ከተማ አካባቢ በሚገኝ ቶሌ ቀበሌ ላይ ሰላማዊ በሆኑና ምንም በማያውቁ ንፁሃን ህፃናትና ሲቪሊያን ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና በርካቶችን መግደላቸውንም ነው ግብረ ኃይሉ ያስታወሰው።
የዚህ ድርጊት ዓላማ፤ ህዝብ በመንግስት ላይ ተስፋ ቆርጦ እንዲነሳና ሰላም እንዲደፈርስ ለማድረግ ነው ያለም ሲሆን "ከድርጊቶቹ ጀርባ እኩይ ዓላማውን በጦርነት ማሳካት ያልቻለው ወያኔ" እንዳለ በመጠቆም ህግ የማስከበር ስራ እየተሰራ ባለበት በዚህ ወቅት አንድ መሆን እንጂ ውዥንብር ውስጥ መግባትና መከፋፈል በፍፁም አይኖርብንም ሲል አስታውቋል፡፡
ግብረ ኃይሉ በተለይ አሸባሪው ህወሓት እና "ፋይናንስ የተደረጉ ሚዲያዎች" የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በብሄርና በሀይማኖት በመከፋፈል ግጭት እንዲፈጠር ለማነሳሳት ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ነው ያለው በመግለጫው።
ሚዲያዎቹ ከአሁን ቀደምም በጎንደር ችግር ከመፈፀሙ አስቀድመው ህዝቡን በሀይማኖት ለመከፋፈል አጀንዳ ቀርፀው ሰላም ለማደፍረስና ግጭት ለማቀጣጠል ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
የተፈጠረው ግጭት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲዳረስና የእምነቱን ተከታዮች ወደ ለየለት ሁከትና ብጥብጥ ለማስገባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረምም ነው ግብረ ኃይሉ ያለው።
ሆኖም የጥፋት ተልዕኳቸው "በህዝባችን የመቻቻል ባህል፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ትዕግስት እና በፀጥታ ኃይሎቻችን ከፍተኛ ርብርብ ከሽፏል" ብሏል።
ሚዲያዎቹ ሰሞኑንም "እንደለመዱት" በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያነጣጠረ ግጭት ለማስነሳት በማሰብ "በአማራ ክልል ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የኦሮሞ እና የሌሎች ብሄር ተማሪዎችን ለማጥቃት የተደራጀ የደህንነት ቡድን ወደ አማራ ክልል ተልኳል" የሚል መልዕክት መስተላለፋቸውንም ነው የገለጸው።
ሆኖም ይህን እየሰሩ ያሉት የትኞቹ ሚዲያዎች እንደሆኑ በውል አላስቀመጠም፡፡
ነገር ግን የተፈጠረውን ክስተት እንደ ሽፋን በመጠቀም በሽብርተኞች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ተጠናክሮ እንዳይቀጥል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኙ ያስታወቀው ግብረ ኃይሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እና ማህበረሰቡ ሴራውን እና አካሄዱን በመረዳት ራሳችሁን በመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
ማሳሰቢያውን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ነው ግብረ ኃይሉ ያስታወቀው፡፡