"ምክር ቤቱ የውይይትና የምክክር እንጂ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ መሆን የለበትም" - የጽ/ቤቱ ኃላፊዎች
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክር ቤቱ የውይይትና የምክክር እንጂ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ መሆን የለበትም አለ።
ጽህፈት ቤቱ ከሰሞኑ "በተወሰኑ የምክር ቤት አባላት" የተስተዋለው ድርጊት የምክር ቤቱን ደንብና አሰራር "ያላከበረ ነው" ሲል ገልጿል።
የምክር ቤቱ የሕግ ጥናት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም ውበት እና የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ፀሐፊ ሔኖክ ሥዩም (ዶ/ር) ሰሞኑን በምክር ቤቱ የተስተዋለውን ሁኔታ በማስመልከት ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያው አቶ ኤፍሬም በምክር ቤቱ አሰራር መሰረት አጀንዳ ማመንጨት፣ አጀንዳ አቀራረብና አመዳደብን ጨምሮ አጠቃላይ የአሰራርና ስነ ምግባር ደንብና መመሪያ መኖሩን ገልጸው አባላቱ የሚመሩበት የአሰራርና የስነ ምግባር ደንቦች እና ከ40 ያላነሱ መመሪዎች እንዳሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ምክር ቤቱ፤ የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብን ተከትሎ የውይይትና የምክክር እንጂ የፖለቲከ ነጥብ ማስቆጠሪያ መሆን የለበትም ብለዋል።
በምክር ቤቱ አሰራርና ስነ ምግባር ደንብ መሰረት አጀንዳ የሚመነጨው በመንግስት፣ በአማካሪ ኮሚቴ፣ በአፈ ጉባዔና በአባላቱ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከሚመነጩ አጀንዳዎችም በአፈ ጉባዔው የሚመራና የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትንም ያካተተ አማካሪ ኮሚቴው ተወያይቶ ካጸደቀው አጀንዳው ከ48 ሰዓት በፊት ለምክር ቤቱ አባላት እንዲያውቁት ተደርጎ በምክር ቤቱ ውይይት እንደሚደረግበት ገልጸዋል።
በአሰራር ደንቡ አንቀፅ 33 መሠረት በዕለታዊ አጀንዳ ያልተቀረፀ ነገር ግን የአፈ ጉባኤውን ፈቃድ ያገኘ ለሕዝብ ጠቀሜታ ያለው አስቸኳይ ጉዳይ በአባላት ወይም በፓርላማ ቡድን ቀርቦ ውይይት ሊደረግበት እንደሚችል ገልጸዋል።
በምክር ቤት የአጀንዳ አቀራረፅ ለመወሰን በወጣ መመሪያ አንቀጽ ዘጠኝ 'ሐ' መሰረት በምክር ቤቱ አማካሪ ሳይጸድቁ የሚቀርቡ አጀንዳዎች መካከልም "የሞቱ አባላትን ወይም የመንግስት ባለስልጣናትን ወይም የታዋቂ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ማቅረብ እና የህሊና ፀሎት እንዲደረግ መጠየቅ" የሚል ይገኝበታል።
በአሰራር ደንቡ አንቀጽ 33 መሰረት ደግሞ "የአፈ ጉባዔው ፈቃድ ያላገኘ ሞሽን ወደ ምክር ቤቱ አይቀርብም፤ አፈ ጉባዔውም ሞሽኑን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ለመግለጽ አይገደደም" ይላል።
የምክር ቤት አባላት የሚያቀርቡት አስቸኳይ አጀንዳ ካለም ስብሰባው ከመጀመሩ ከ10 ሰዓት በፊት ለአፈ ጉባዔው መቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል ብለዋል።
የፅህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ፀሐፊ ሔኖክ ሥዩም (ዶ/ር) በበኩላቸው ምክር ቤቱ ከሌሎች ሃገራት ጭምር በተሞክሮነት የወሰዳቸው አገራዊ ውይይቶች፣ ምክክሮችና ውሳኔዎች የሚተላለፉበት የራሱ አሰራር እንዳለው ገልጸው ምክር ቤቱ "ውይይትና ምክክር የሚካሄድበት እንጂ የፖለቲካ ነጥብ ማስቆጠሪያ መሆን የለበትም" ብለዋል።
ዋና ጸሐፊው በየትኛውም የአገሪቷ ክፍሎች የሚያጋጥሙ ችግሮች የሁሉም የምክር ቤት አባላት ጉዳይ ቢሆኑም ጥያቄዎች ግን በአሰራርና ደንቡ መሰረት አድርጎ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።
ግድፈት ያሳዩ የምክር ቤቱ አባላት የሚጠየቁበት አሰራር እንዳለ ገልጸው፤ ምክር ቤታዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ግን ምክር ቤቱ አይመለከተውም ሲሉ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ የምክር ቤቱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ምክር ቤቱ ወለጋ ላይ የተገደሉ ዜጎችን ጉዳይ በአጀንዳነት እንዲይዝ ጠይቀው ነበር።
ሆኖም የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ጠያቂው እንዲናገሩ አለመፍቀዳቸውን በማሳወቅ ጥያቄውን ሳይቀበሉ ቀርተዋል። በዚህም ዶ/ር ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የአብን የምክር ቤት አባላት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ዶ/ር ደሳለኝ ለአፈ ጉባዔው አጀንዳ እንዲያዝላቸው ያቀረቡበት መንገድ ከምክር ቤቱ ስነ ምግባር፣ አሰራርና ሕግ ያፈነገጠ ነው ያሉት ዋና ጸኃፊው በደንቡ መሰረት አጀንዳ ቀደም ብሎ ለምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ፣ ለመንግስት ተጠሪ ወይም ለሚመለከተው መንግስታዊ አካል መቅረብ እንዳለበት ቢደነገግም አባሉ እንዳላቀረቡ ተናግረዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ በወቅቱ በአፈ ጉባኤው ሲገለጽ እንደነበረው የምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አባል ናቸው። በዚህም አጀንዳዎችን ለኮሚቴው ማቅረብ ይችሉ ነበር እንደ ዶ/ር ሔኖክ ገለጻ።
በሌላ በኩል ወቅታዊ ጉዳዮች ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ለአፈ ጉባዔው ቀርበው በአጀንዳነት ሊያዙ የሚችሉበት አሰራር ቢኖርም ዶ/ር ደሳለኝ ቀድመው ይህን እንዳላደረጉና ጉዳዩን በአጀንዳነት እንዳላስያዙ ተናግረዋል።
በዚህም በደንቡ መሰረት ያልቀረበን ጥያቄ ያለ መቀበልና ጥያቄ ያልተቀበሉበትን ምክንያት ያለመግለጽ ሕጋዊ መብት ያላቸው አፈ ጉባዔው ጥያቄውን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ይህ የአፈ ጉባኤው ውሳኔ ትክክል እንደነበርም ነው የጽህፈት ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ያነሱት።
ከምክር ቤቱ ደንብና አሰራር ድንጋጌ አንጻር ጉዳዩ ተገቢነት እንደሌለውም ተናግረዋል።
ስብሰባውን ረግጠው የወጡት የምክር ቤቱ የአብን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በንጹሃን ግድያ ዙሪያ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ መስጠት አለባቸው ሲሉ መጠየቃቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል።