የምክክር ኮሚሽነሮች ምርጫ ላይ በሙስና ተከሰው የነበሩና የውጭ ሀገር ዜጎች መካተታቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ገለፀ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኮሚሽኑ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲሻሻሉ እንጂ ሂደቱ እንዲቆም እንደማይፈልግ ገልጿል
“ሀገራዊ ምክክር” የሚለው ሃሳብ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት “ቀድሞ አስቦት ነበር” ተብሏል
ገዥው ፓርቲ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ “ለኮሚሽነርነት የሚያበቁ መሥፈርቶች” በሚል የቀረበው መስፈርት እየተጣሰ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ራሄል ባፌ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የምክክር ኮሚሽኑን ለማቋቋም የተደረገው ሂደት ግልጽነት የጎደለው፣ ገለልተኛ እና አካታች አለመሆኑን አንስቷል። በዚህም መሰረት ምክር ቤቱ ቅሬታውን ለሚመለከታቸው ተቋማትና ግለሰቦች እንዳቀረበ ገልጿል።
“ማንኛውም ኮሚሽነር ሆኖ የሚሾም ሰው ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ፣ ለሀገራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋፅዖ ሊያበረክት የሚችል፣ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው፣ በከባድ ወንጀል ተከሶ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተላለፈበት“ የሚል ይዘት ያለው ቢሆንም፤ አሁን የተጀመረው የኮሚነሮች የምርጫ ሂደት ግን ከነዚህ መስፈርቶች ያፈነገጠ እንደሆነ ምክር ቤቱ ገልጿል።
ሰብሳቢዋ ፤ በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ውስጥ በኃላፊነት እንዲሰሩ ጥቆማ ከተደረገላቸው 632 ሰዎች ውስጥ 42 ሰዎች የተመረጡበት ሂደት ግልጽነት የጎደለው እንደሆነ ገልጸው፤ ይህ ሂደት በአስቸኳይ መስተካከል እንዳለበት አንስተዋል።
ሕዝብ ጥቆማ የሰጠባቸው 632 ግለሰቦችም እነማን እንደሆነ ግልጽ መደረግ እንዳለበት የገለጹት ሰብሳቢዋ የተጠቆሙት ሁሉም ሰዎች ዝርዝር ይፋ መሆን፤ ሕዝብ ጥርጣሬ እንዳይገባው ያደርጋል ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም ከ 632 ሰዎች ውስጥ የተመረጡት 42 ሰዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆኑ እንዲሁም በከባድ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰቦች እንዳሉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያሉትን ቅሬታዎች ለሚመለከታቸው ተቋማት ማቅረቡን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ሀጋዊ ምክክሩን በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ጋር መወያየቱን የጠቀሱት ዶ/ር ራሄል የቅሬታ ደብዳቤዎችን ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ለሌሎች አካላት ማስገባቱን ገልጸዋል።
ሰብሳቢዋ፤ ቀደም ሲል የምክክር ኮሚሽኑ አዋጅ ላይ አስተያየት ለመስጠት ረቂቁን አቅርበው ከነበሩት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር ) ጋር 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት አድርገው እንደነበር ገልጸዋል። ውይይት በተደረገበት ወቅት መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች እንዲሻሻሉ ሃሳብ “ብንሰጥም ሊካተት አልቻለም” ብለዋል።
አሁን ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክሩ እንዲቆም እንደማይገፈልጉ ያነሱት ሰብሳቢዋ ፤ የም/ቤቱ ፍላጎት ግን ችግሮች ተስተካክለው ሂደቱ እንዲቀጥል ነው ብለዋል።
ከ42 ዕጩዎች ውስጥ አራቱ ብቻ ሴቶች መሆናቸው፤ ሴቶችና ወጣቶችን በስፋት አለማካተቱ ራሱን የቻለ ጉድለት እንደሆነም ተነግረዋል።
ሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን ከመቋቀቋሙ በፊት የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን ለማድረግ ዕቅድ እንደነበረውም ዶ/ር ራሄል ጠቅሰዋል።