“የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ተጠፍጥፎ የሚቀመጥለትን አሻንጉሊት መንግስት አይቀበልም”- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወቅት በተለይ የትግራይ ተወላጆች ላይ እንግልት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል
ጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ቅድሚያ እንዲሰጥም ምክር ቤቱ ጠይቋል
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ የአስፈፃሚ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት በዛሬው እለት አስቸኳይ ጉባዔ ካደረጉ በኋላ መግለጫ አውጥተዋል።
በመግለጫውም “በከፍተኛ የህዝብ ትግል እና መስዋዕትነት የተገኘውና ባለፉት ሶስት ዓመታት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የዘለቀውን የለውጥ ሂደት የከፋ ፈተና ውስጥ የከተተው የዛሬ ዓመት በህወኃት የተፈፀመው የክህደት ተግባር ነው” ብሏል።
ይህንን ተከትሎ ሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረው ጦርነት ሰፍቶ በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል ልዩ ልዩ ቦታዎች የከተማ እና የገጠርን ህዝብ ለከፋ ምስቅልቅል ዳርጓል ያለው ምክር ቤቱ፤ ጊዜው የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት መሆኑ ደግሞ እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል።
“በሰሜን አሜሪካ ፌደራሊስት/ኮንፌደራሊስት ጥምረት ፈጠርን ብለው በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት በተፈረጀው ህወኃት አቀናባሪነት ሲንደፋደፉ የታዩትን ግለሰቦችም ታዝበናል” ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።
“የኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ መርጦ የሚያቆመው እንጂ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ተጠፍጥፎ የሚቀመጥለትን አሻንጉሊት መንግስት በታሪክ ተቀብሎ አያውቅም፣ ዛሬም አይቀበልም” ያለው ምክር ቤቱ፤ የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ጥምረት እንደማይቀበልም አስገንዝቧል።
ምር ቤቱ አክሎም በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ በተለይ የቀድሞ ሰራዊት አባላትና የውትድርና ስልጠና ያላቸው ሁሉ ነቅቶና ተደራጅቶ ሀገሩ የምትጠይቀውን ሁሉ መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን ከውጭም ሆነ ከውስጥ ችግር ፈጣሪዎች እንዲጠብቅ ጥሩ አቅርቧል።
በዚህ ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት ቅድሚያ እንዲሰጥ የተየቀው ምክር ቤቱ፤ ሁሉም ዜጎች በሙሉ ኃይል እንዲረባረብም ጠይቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ንፁሐን ዜጎች (በተለይ የትግራይ ተወላጆች) ላይ እንግልት እንዳይደርስ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግም ምክር ቤቱ አሳስቧል።
መንግሥት ከሀገራዊ መግባባት መድረኩ ገለልተኛ ሆኖ ሂደቱ የሚጀመርበትን እና የሚፋጠንበትን ሁኔታ በማመቻቸት ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባልም ብሏል።
ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የ21ኛውን ክፍለ ዘመን በሚመጥን ደረጃ የሃሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት እንዲዘጋጁም ምክር ቤቱ ጥሪ አስተላፏል።