በዮርዳኖስ የንጉሳዊያን ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ
በሀገሪቱ “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” መደረጉ ቢገለጽም ፣ ኋላ ላይ ግን መንግስት እርምጃው “ከደህንነት ጋር የተያያዘ ነው” ብሏል
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሀገሪቱን ስልጣን ለመቆጣጠር በማሴር የተጠረጠሩ ናቸው ተብሏል
ቅዳሜ እለት የጆርዳን የፀጥታ ሃይሎች እ.ኤ.አ ከ 1999 ጀምሮ ዮርዳኖስን ከሚያተዳደሩት ንጉስ አብደላህ ዳግማዊ ፣ ስልጣን ለመቀማት በማሴር የተጠረጠሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል፡፡
የጆርዳን መንግስት የንጉሳዊ ቤተሰብ አባል እና የቀድሞው የንጉሳዊ ቤተመንግስት ዋና ኃላፊን ጨምሮ በመንግስቱ ውስጥ ከፍተኛ ስም ያላቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ባለስልጣናት ቅዳሜ ማታ በሀገሪቱ ተፈጽሟል የተባለውን ሴራ እና የ “ዮርዳኖስን ደህንነት እና መረጋጋት” ለሰዎቹ መታሰር በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት እና ዳግማዊ ንጉስ አብደላህ ለረጅም ጊዜ ይተማመኑባቸው የነበሩት ባሲም አዋዳላህ እንዲሁም በሳዑዲ አረቢያ የቀድሞው የንጉሳዊ ልዑክ የነበሩት የንጉሣዊው ቤተሰብ አባል ሻሪፍ ሀሰን ቢን ዛይድ ከሌሎች ስማቸው ካልተጠቀሱ ሰዎች ጋር ተይዘዋል፡፡
የአብደላህ ግማሽ ወንድም ፣ የቀድሞው ዘውዳዊ ልዑል ሀምዛ ቢን ሁሴንም በወንጀሉ ተጠርጥረው የቤት ውስጥ እስረኛ መሆናቸውን ፣ትናንት በለቀቁት ቪዲዮ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንዳልታሰሩ የተናገሩት የጸጥታ ኃይሎች ፣ በምትኩ “የዮርዳኖስን መረጋጋት እና ደህንነት ሊያናውጡ የሚችሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን እንዲያቆሙ” መታዘዛቸውን አስታውቀዋል፡፡
የ 59 ዓመቱ ንጉስ አብደላህ ፣ አባታቸው ንጉስ ሁሴን ከሞቱ በኋላ እ.ኤ.አ በ1999 ነው ዙፋኑን የተረከቡት፡፡ የአሁኑ የዘውድ ልዑል ደግሞ የ26 ዓመት ልጃቸው ሁሴን ቢን አብደላ ናቸው፡፡
ሀምዛ ከሶሪያዊ አሜሪካዊ ቤተሰብ የተወለዱ እና የንጉስ ሁሴን እና የአራተኛ ባለቤታቸው ንግስት ኑር የበኩር ልጅ ሲሆኑ እ.ኤ.አ. በ 1999 የዮርዳኖስ ዘውዳዊ ልዑል ሆነው ተሹመው ነበር፡፡ ነገር ግን ግማሽ ወንድማቸው አብደላህ የማዕረግ ስሙን በ 2004 ለልጃቸው አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡
ሀምዛ ብዙውን ጊዜ ከጎሳ መሪዎች ጋር በመገናኘት ይታወቃሉ፡፡ ይህም ከአባታቸው ጋር የሚያመሳስላቸው እና በብዙዎች ዘንድ እንዲወደዱ ያደረጋቸው ተግባር ነው፡፡ የአሁኑ ንጉስ ይህን ድርጊታቸውን የማይወደው ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ስልጣን ለመቀማት አሲረዋል ካላቸው ግለሰቦች ጋር ፈርጇቸዋል፡፡ ይሁንና የቀድሞው ልዑል ሀምዛ በምንም አይነት የሴራ ድርጊት አለመሳተፋቸውን ገልጸው ውንጀላው የስርዓቱ የተለመደ ድርጊት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዮርዳንስ ተፈጽሟል የተባለውን “የመፈንቅለ መንግስት ሴራ” በርካታ የአረብ ሀገራት እና እስራኤል አውግዘዋል፡፡ የሀገሪቱ መንግስት የወሰደውን እርምጃም ደግፈዋል፡፡