በኒጀር የተሞከረ መፈንቅለ መንግስት መክሸፉ ተገለጸ
መፈንቅለ መንግስቱ የተሞከረው አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝደንት ቃለ መሀላ ሊፈፅሙ ሁለት ቀናት ሲቀሯቸው ነው
በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የተሳተፉ በርካታ ግለሰቦች መያዛቸውን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል
በኒጀር መዲና ኒያሚ ዛሬ መፈንቅለ መንግስት ተሞክሮ መክሸፉን የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡
ማለዳ ላይ በፕሬዝዳንቱ መኖርያ ቤት አካባቢ ከባድ የተኩስ ድምፅ መሰማቱ የተገለጸ ሲሆን ሁኔታው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንደነበር የሀገሪቱ መንግስት ቃል አቀባዩ አብዱራህማን ዛካሪያ አስታውቀዋል፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ የተሞከረው ተመራጩ ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም ቃለ መሀላ ሊፈፅሙ ሁለት ቀናት ብቻ ሲቀሯቸው ነው፡፡
ቃል አቀባዩ አብዱራህማን ዛካሪያ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የተሳተፉ በርካታ ግለሰቦች መያዛቸውን ስለመግለጻቸው ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
በሀገሪቱ ተሞክሮ የነበረው መፈንቅለ መንግስት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
በመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራው እጃቸው እንዳለ ከተጠረጠሩ የኒጀር ጦር አባላት መካከል የተወሰኑት መታሰራቸውንም ቃል አቀባዩ ይፋ አድርገዋል፡፡
በሀገሪቱ መዲና ኒያሚ ጠዋት ላይ ከባድ የተኩስ ድምጽ የተሰማ ሲሆን ይህም ለ30 ደቂቃዎች መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ባዙም የካቲት ለይ በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ ቢሆንም፣ የቀድሞ ፕሬዝደንት ማሃማኔ ኦስማን ግን ውጤቱን እንደማይቀበሉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህም ሀገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ አስገብቷት እንደነበር በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ የኢስላማዊ ታጣቂዎች ለኒጀር ሌላኛው ፈተና መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከነገ በስቲያ ቃለ መሀላ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል፡፡