ፕሬዝደንት ትራምፕ "ዩክሬን አንድ ቀን የሩሲያ ልትሆን ትችላለች" ሲሉ ተናገሩ
ትራምፕ ጦርነቱ የሚቆምበትን እቅድ እንዲያዘጋጅ የተመደበውን ልዩ መልእክተኛቸውን በቅርቡ ወደ ዩክሬን እንደሚልኩ በትናንትናው አረጋግጠዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/11/243-131109-images-5-_700x400.jpeg)
ትራምፕ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የሚፈልጉ ሲሆን ዩክሬን ስምምነት ላይ ከመድረሷ በፊት ከአሜሪካ የደህነት ዋስትና ትፈልጋለች
ፕሬዝደንት ትራምፕ "ዩክሬን አንድ ቀን የሩሲያ ልትሆን ትችላለች" ሲሉ ተናገሩ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ምክትላቸው ዲጄ ቫንስ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን ለማግኘት እየተወጋጁ በሚገኙበት ወቅት "ዩክሬን የሆነ ቀን የሩሲያ ልትሆን ትችላለች" ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ ይህን ያሉት ሶስት አመት ገደማ ያስቆጠረውን የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ በተመለከተ ከፎክስ ኒውስ ጋር ቃል ምልልስ ባደረጉት ወቅት ነው።
ትራምፕ "ስምምነት ላይ ሊደርሱ ወይም ላይደርሱ ይችላሉ፤ የሆነ ጊዜ የሩሲያ ሊሆኑ ወይም ላይሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።
ከሩሲያ ጋር እየተዋጋች ላለችው ዩክሬን ብዙ ገንዘብ ፈስስ ማድረጋቸውን የገለጹት ፕሬዝደንት ትራምፕ ዩክሬን እንድትከፍላቸው ይፈልጋሉ።
"ከ500 ቢሊዮ ዶላር ጋር የሚስተካከል ዋጋ ያለው ብርቅ ማዕድናት እንደምፈልግ ነግሬያቸዋለሁ" ብለዋል። ትራምፕ እንዳሉት ዩክሬንም በዚህ ሀሳብ ተስማምታለች።
ትራምፕ ጦርነቱ የሚቆምበትን እቅድ እንዲያዘጋጅ የተመደበውን ልዩ መልእክተኛቸውን በቅርቡ ወደ ዩክሬን እንደሚልኩ በትናንትናው አረጋግጠዋል። ትራምፕ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የሚፈልጉ ሲሆን ዩክሬን ደግሞ ጦርነቱ እንዲቆም ስምምነት ላይ ከመድረሷ በፊት ከአሜሪካ የደህነት ዋስትና ትፈልጋለች።
የኪቭ የኔቶ አባል መሆን ወይም የሰላም አከስከባሪ ማሰማራትን የማያካትት ማንኛውም ስምምነት ሞስኮ ራሷን አጠናክራ አዲስ ጥቃት እንድትፈጽም የሚያደርግ በመሆኑ እንደማትቀበለው መግለጿ ይታወሳል።
የፕሬዝደንት ዘለንስኪ ቃል አቀባይ ሰርጊ ኒኪፎሮግ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት በመጭው አርብ እለት ከቫንስ ጋር እንደሚገናኙ ተዘግቧል።
ትራምፕ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ የሚቋጭ እቅድ እንዳላቸው በተጋጋሚ ቢናገሩም ይዘቱን ግልጽ አላደረጉም።
ፑቲን ዩክሬን ከደቡብና ከምስራቅ ይዞታዎች ለቃ እንድትወጣና ወደ ኔቶ እንዳትገባ እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ዩክሬን ምንም አይነት ግዛት አሳልፋ እንደማትሰጥ አቋም ይዛለች።
ዘለንስኪ ችግሩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲቋጭ ከፑቲን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ፍቃደኝነታቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ዘለንስኪና ፑቲን አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በቀጥታ ንግግር ለማድረግ አንደማይፈልጉ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ወደ ኋይትሀውስ እንደገቡ ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ቃል ገብተው የነበረት ፕሬዝደንት ትራምፕ ጦርነት በሚቆምበት ጉዳይ ከፑቲን ጋር መነጋገራቸው ይፋ አድርገዋል። ነገርግን ትራምፕ ከፑቲን ጋር በስልክ ስለተነጋገሯቸው ጉዳዮች ፍንጭ ከመስጠት ውጭ ዝርዝሩን ገልጽ አላደረጉም።
የሩሲያ ቤተመንግስት ክሬሚሊንም ቢሆን ሁለቱ መሪዎች ስለመነጋገራቸው ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል አልፈለገም።