ጋዜጠኛ ታምራት በትናንትናው እለት ፍርድ ቤት መቅረቡን ባለቤቱ ወይዘሮ ሰላም በላይ ገልጻለች
ተራራ ኔትዎርክ የተሰኘ የኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ተላልፎ በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ ፖሊስ መምሪያ እንደታሰረ ባለቤቱ ተናገረች፡፡
ጋዜጠኛው ላለፉት ስምንት ቀናት የት እንዳለ ሳይታወቅ መቆየቱን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን በኦሮሚያ ክልል ፈላን ከተማ እንደሚገኝ ባለቤቱ አረጋግጣለች፡፡
- ጋዜጠኛ ታምራት የት እንደታሰረ ለማወቅ በፍለጋ ላይ መሆኗን ባለቤቱ ገለጸች
- ኢሰመኮ መንግስት ጋዜጠኞቹ የታሰሩበትን ቦታ እንዲያሳውቅ ጠየቀ
- የኦቢኤን ጋዜጠኛ በታጣቂዎች ተገደለ
በትናንትናው ዕለት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ፍርድ ቤት መቅረቡን ባለቤቱ ወይዘሮ ሰላም በላይ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጻለች፡፡ በፊንፊኔ ዙሪያ የገላን ከተማ ፍርድ ቤትም ለጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የ14 ቀን ቀጠሮ እንደሰጠውም ባለቤቱ ተናግራለች፡፡
ከመኖሪያ ቤቱ በፖሊስ ከተወሰደ አንድ ሳምንት ያለፈው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ያለበት የታወቀው በታሰረ በ7ኛ ቀኑ እንደሆነም ነው ባለቤቱ ያስታወቀችው፡፡
ጋዜጠኛው ትናንት ካለጠበቃ በኦሮሚያ ክልል ገላን ፍርድ ቤት ቀርቦ የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀበትም ባለቤቱ ወ/ሮ ሰላም በላይ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቃለች፡፡ የተራረ ኔትዎርክ ዋና አዘጋጅ ታምራት ነገራ በ ፌዴራል ፖሊስ ቢያዝም ፤ ለኦሮሚያ ፖሊስ ተላልፎ እንደተሰጠ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ እና ክብሮም ወርቁ የታሰሩበት ቦታ አለመታወቁን እንደሚያሳስበው ትናንትና መግለጹ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ በጥቅሉ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን ጉዳይ እየተከታተሉት መሆኑን ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ለአል ዐይን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ባለቤት ወይዘሮ ሰላም በላይ ባለቤቷ የት እንደታሰረ የሚነግራት አካል እንዳላገኘች ከሰሞኑ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግራለች፡፡ ቤተሰቦቹ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን የገለጸችው ሰላም ከቤቱ ከተወሰደ አንድ ሳምንት ቢቆጠርም እስካሁን ድረስ የት እንደታሰረ ማወቅ እንዳልተቻለ ገልጻ፤ ታምራት የት እንዳለ ባለመታወቁ ቤተሰቦቹ ምግብ፣ ልብስና መድሃኒት ሊያደርሱለት እንዳልቻሉም መግለጿ ይታወሳል፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ የነበረ ሲሆን በስራው ምክንያትም ከሀገር እንዲሰደድ ተገዶ በአሜሪካ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ጋዜጠኛው ባለፈው አርብ ከጠዋቱ 4 ሰዓት 30 ላይ “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” በሚል ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱ ይታወሳል፡፡