የኢሰመኮ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል የጋዜጠኞቹን እስር ጉዳይ ኢሰመኮ እየተከታተለው መሆኑን ገልጸዋል
“ተራራ ኔትዎርክ” የተሰኘ የኦንላይን ሚዲያ ዋና አዘጋጅ፣ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በፖሊስ ከመኖሪያ ቤቱ ቢወሰድም እስካሁን ያለበት ቦታ አለመታወቁን ባለቤቱ ተናግራለች፡፡
የጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ባለቤት ወይዘሮ ሰላም በላይ ባለቤቷ የት እንደታሰረ የሚነግራት አካል እንዳላገኘች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግራለች፡፡
ቤተሰቦቹ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን የገለጸችው ሰላም ከቤቱ ከተወሰደ አራተኛ ቀኑ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የት እንደታሰረ ማወቅ እንዳልተቻለ ተናግራለች፡፡ ታምራት ነገራ የት እንዳለ ባለመታወቁ ቤተሰቦቹ ምግብ፣ ልብስና መድሃኒት ሊያደርሱለት እንዳልቻሉም ባለቤቱ ሰላም በላይ ለአል ዐይን ተናግራለች።
ጋዜጠኛው ባለፈው አርብ ዕለት ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ ቤተሰቦቹ ወደዚያው አቅንተው ለማየት ቢጠይቁም የታሰረበትን ትክክለኛ ቦታ የሚነግራቸው እንዳጡ ሰላም ተናግራለች፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ጉዳዩን የያዘው “የኦሮሚያ ፖሊስ ነው” በመባሉ ቤተሰቦቹ ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ መምሪያ ከዚያም ግሎባል ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሄዱም ታምራት ወደ ሁለቱም ቦታዎች እንዳተወሰደ ነው የተገለጸው፡፡
የታምራት ቤተሰቦች “ወደ ቡራዩ እና ገላን ከተሞች ሄዳችሁ አጣሩ” መባላቸውን ያነሳችው ባለቤቱ ሰላም በቡራዩ ከተማ በሚገኙ ሶስት ፖሊስ ጣቢያዎችና በተጨማሪም ገላን ኮንዶሚኒየም ወደ ሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ቢያቀኑም ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረው ነበር።
በዛሬው ዕለትም ጋዜጠኛው ያለበትን ቦታ ለማጣራት የታምራት ባለቤት ሰላም ወደ ገላን ወንድሟ ደግሞ ወደ ዓለም ገና ከተማ እየሄዱ መሆኑን ጠቅሳለች፡፡
የታምራት ባለቤት በእያንዳንዱ ቦታ ስትሄድ “ለእገሌ ነው የሰጠነው ፤ ለእገሌ ነው” እንዳሏት ገልጻ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም የአስቸኳ ጊዜ መርማሪ ቦርድን ደብዳቤ ይዛ ወደ ገላን እየሄደች መሆኑን ገልጻለች፡፡ አንድ ኢንስፔክተርም “ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ዞራችሁ ፈልጉት” እንዳላት ተናግራለች፡፡
ከጋዜጠኛ ታምራት በተጨማሪም ቀድሞዋ ዓባይ ሚዲያ ባልደረባ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድም እስር ላይ መሆኗ ተገልጿል፡፡ ጋዜጠኛ መአዛ ሮሃ የሚል የራሷ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ከፍታ በመስራት ላይ ነበረች፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ ባወጣው መግለጫ“ጋዜጠኞች በትክክል ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለእስር መዳረጋቸው”በኢትዮጵያ የወደፊት የጋዜጠኝነት ነፃነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖው ያሳድራል ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር እንደሚገነዘብ የገለጸው ማህበሩ የታሰሩ ጋዜጠኞች ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁን እንደሚያወግዝና “በህግ ቁጥጥር ስር ያሉት ጋዜጠኞች ተገቢው የህግ ከለላና ፍትህ”እንዳያገኙ ያደርጋል ብሏል፡፡
ማህበሩ መንግስት የታሰሩትን ጋዜጠኞች ፍትህ የማግኘት መብት እንዲያከብር ጠይቋል፡፤
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የጋዜጠኞቹን እስር እየተከታተሉት መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ቀደም ባለው ጊዜ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ የነበረ ሲሆን በስራው ምክንያትም ከሀገር እንዲሰደድ ተገዶ በአሜሪካ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ጋዜጠኛው ባለፈው አርብ ከጠዋቱ 4 ሰዓት 30 ላይ “ለጥያቄ ትፈለጋለህ” በሚል ከመኖሪያ ቤቱ መወሰዱ ይታወሳል፡፡