ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ራሳቸውን ‘አባ ቶርቤ’ ብለው በሚጠሩ የሸኔ አባላት ትናንት አመሻሽ መገደሉን ፖሊስ አስታውቋል
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ በታጣቂዎች መገደሉ ተሰማ።
ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ በትናትናው እለት በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ “የሸኔ ታጣቂዎች በፈጸሙበት ጥቃት” ህይወቱ ማለፉን ኦቢኤን የአካባቢውን ፖሊስ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በቄለም ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ሰላም ማረጋገጥ ዳይሬክተር ኢንስፔክተር አህመድ ያሲን እንዳስታወቁት፤ ጋዜጠኛው ትናንት ምሽት ሰርግ ለይ ውሎ ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ እያለ ግድያው በሁለት ሰዎች ነው የተፈጸመበት።
ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ራሳቸውን ‘አባ ቶርቤ’ ብለው በሚጠሩ የሸኔ አባላት ትናንት አመሻሽ 11:30 ገደማ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ መገደሉንም ነው ኢንስፔክተር አህመድ ያስታወቁት።
ግድያውን የፈጸሙ ሁለቱን ግለሰቦች በስም መለየቱን እና በአሁኑ ወቅትም ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እያደረገ መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል።
ጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የቄለም ወለጋ ዞን ጋዜጠኛ እና አስተባባሪ እንደነበረ ተቋሙ አስታውቋል።
በጋዜጠኛ ሲሳይ ፊዳ ላይ ተፈጸመው ግድያ እንዳሳዘነው ያስታወቀው ኦቢኤን ተግባሩ ጣቢያው ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት “የሚያጠናክር እንጂ ወደኋላ የሚመልስ አይደለም” ብሏል።
ህብረተሰቡ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቋማት ተግባሩን እንዲያወግዙትም ኦቢኤን ጥሪ አቅርቧል።
ባሳለፍነው ሃሙስ መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሸኔን እና ህወሓትን “ሽብርተኛ” ሲል መፈረጁ የሚታወስ ነው፡፡