በሃምሌ ወር የተመዘገበው የሙቀት መጠን ከ1880ዎቹ ወዲህ ከነበሩ 1700 ወራት ሁሉ የላቀ ነው ተብሏል
ሃምሌ ከየትኛውም የዓመቱ (2021) ወር ሞቃታማ እንደነበር የአሜሪካ ብሔራዊ የአካባቢያዊ መረጃ ማዕከል አስታወቀ፡፡
ማዕከሉ ሃምሌ በተለምዶ ከፍተኛ ሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ወር ቢሆንም ያለፈው ወር ግን እ.ኤ.አ ከ1880ዎቹ ወዲህ ከነበሩ 1700 ወራት ሁሉ የላቀ የሙቀት መጠን የተመዘገበበት ሞቃታማ ወር ነበር ብሏል፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢያዊ አየር መረጃ አስተዳደር ሪክ ስፒንራ " ባለፈው ሃምሌ ወር የተመዘገበው የሙቀት መጠን አዲስ ሪከርድ ነው፤ ይህም በዓለም ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ የሚያባብስ ነው" ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራባዊ አሜሪካ፣ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤስያ ክልሎች ውስጥ በወሩ ውስጥ በርካታ የሙቀት ሞገዶች መታየታቸውንም ነው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በተመድ የአየር ንብረት ለውጥን ጉዳይ የሚመለከተው የመንግሥታት ፓነል /IPCC/ ለዓለማችንን ከፍተኛ ሙቀት መጨመር የሰው ልጆች ሚና እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ እንዲሁም ጉዳቶቹን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት አውጥቷል፡፡
ሪፖርቱ አክሎ “ያለፉት አራት አስርት ዓመታት እያንዳንዳቸው እ.ኤ.አ ከ 1850 ጀምሮ ከነበሩት አስርት ዓመታት የበለጠ ሞቃታማ ነበሩ" ብሏል
በሞቃታማ ዓለም እና እየከፋ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ መካከል ቀጥተኛ ቁርኝት መኖሩም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡