በሩዋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ አሸነፉ
እስካሁን ከተቆጠረው 79 በመቶ ድምጽ ካጋሜ 99 ነጥብ 15 በመቶውን ማግኘታቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል
ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር ከ2000 ጀምሮ በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት ካጋሜ በምርጫው ተቀናቃኞቻቸውን ከፉክክር አስወጥተዋል በሚል ይወቀሳሉ
በትናንትናው እለት በተካሄደው የሩዋንዳ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፖል ካጋሜ በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፋቸው ተነገረ።
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እስካሁን ከተቆጠረው 79 በመቶ ድምጽ ካጋሜ 99 ነጥብ 15 በመቶውን ማግኘታቸውን ይፋ አድርጓል።
የ66 አመቱ ፕሬዝዳንት በስልጣን ላይ ለ29 አመት የሚያቆያቸውን ድምጽ ማግኘታቸው የሚጠበቅ ነበር የሚለው ሬውተርስ፥ ዲያን ርዊጋራን ጨምሮ ሶስት ብርቱ ተቀናቃኞቻቸውን ከምርጫ ፉክክሩ ውጭ መሆናቸውን ያወሳል።
በምርጫው የተሳተፉት የአየር ንብረት ጥበቃ ተሟጋቹ ፍራንክ ሃቢኔዝ እና ጋዜጠኛና ደራሲው ፊሊፕ ምፓይማና 1 በመቶ እንኳን መራጭ አለማግኘታቸውንም በመጥቀስ።
እስካሁን በተካሄደው የድምጽ ቆጠራ ሃቢኔዝ 0.53 በመቶ፤ ምፓይማና ደግሞ 0.32 በመቶ መራጭ ማግኘታቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
የምርጫው ከፊል የቆጠራ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በፓርቲያቸው “ሩዋንዳ ፓትሪዮቲክ ፍሮንት” ዋና ቢሮ በመገኘት የሀገሪቱን ዜጎች አመስግነዋል።
ድምጽ የሰጧቸው ሰዎች በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት መጨመሩን እንደሚያሳይ በመጥቀስም “አሃዙ (የመረጧቸው ሰዎች ብዛት) ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የጣሉብን እምነት ማሳያ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
ካጋሜ በ2017ም በተመሳሳይ ተቀናቃኝ በሌለበት ምርጫ 98.8 በመቶ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ቢቢሲ አስታውሷል።
ሩዋንዳ ከ1994ቱ የዘር ፍጅት በኋላ የተረጋጋች ሀገር እንድትሆንና ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ በማድረጉ ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበራቸው ፖል ካጋሜ ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ነው።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ካጋሜ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ የሩዋንዳውያንን ነጻነት ገድበዋል፤ የምርጫ ፉክክር እንዳይኖር አድርገዋል በሚል ይወቅሷቸዋል።
ደጋፊዎቻቸው ግን 1 ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብን የጨረሰውን የጎሳ ክፍፍል አስቀርተው ሁሉም እኩል የሚሆንበትን ስርአት ዘርግተዋል፤ የኪጋሊን ኢኮኖሚም አሳድገዋል በሚል ይከራከሩላቸዋል።
በትናንቱ ምርጫ ለመሳተፍ ብቁ ከነበሩ 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ሩዋንዳውያን 98 በመቶው ድምጻቸውን መስጠታቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ገልጿል።
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው የመጨረሻ ውጤት ከ11 ቀናት በኋላ በይፋ ይገለጻል ተብሏል።