ሩዋንዳ ስደተኞችን ለመቀበል ከብሪታንያ የተሰጣትን 310 ሚሊየን ዶላር አልመልስም አለች
የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሽ ሱናክ ህገ ወጥ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ፕሮግራም ጀምረው ነበር
አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ይህን ፕሮግራም መሰረዛቸውን ተከትሎ ሩዋንዳ የተከፈለኝን ገንዘብ አልመልስም ብላለች
ሩዋንዳ ስደተኞችን ለመቀበል ከብሪታንያ የተሰጣትን 310 ሚሊየን ዶላር አልመልስም አለች።
ሩዋንዳ ከብሪታንያ የሚላኩ ህገወጥ ስደተኞችን ለማስተናገድ የተከፈላትን 310 ሚሊየን ዶላር አልመልስም ብላለች፡፡
የወግ አጥባቂ ፓርቲ እጩው የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሪሽ ሱናክ በሀገሪቱ በርክተዋል የተባሉትን ህገ ወጥ ስደተኞች ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ከፖል ካጋሜ መንግስት ጋር ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡
ይህ እቅድ ይፋ ከተደረገበት 2022 ጀምሮ ለስደተኞች ማቆያ ቅድመ ዝግጅት እና ለሌሎች ተያያዥ ወጪዎች ብሪታንያ ለሩዋንዳ 310 ሚሊየን ዶላር ሰጥታለች፡፡
በቅርቡ በብሪታንያ በተደረገ ምርጫ ጠቅላይ ሚንስተር ሱናክን ተክተው የመጡት ኪር ስታርመር ይህ ፕሮግራም ተግባራዊ እንደማይደረግ አሳውቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ አንዳንድ የፓርላማ አባላት ለሩዋንዳ ወጪ የተደረገው ገንዘብ መመለስ እንዳለበት መጠየቃቸውን የሰማችው ሩዋንዳ በስምምነታችን ውስጥ ገንዘብ መመለስ የሚል ሀሳብ አልተካተተም ብላለች፡፡
የሩዋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ አሊን ሙክራሊንዳ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ “ሀሳቡን አቅርበው የጠየቁን እነርሱ ናቸው ስደተኞችን ለመቀበል እና ለማስተናገድ በዝርዝር ወጪዎች እና ዝግጅቶች ዙርያ ተስማምተን ተፈራርመናል ከስምምነቱ ውስጥ ግን ኪጋሊ ገንዘቡን ለለንደን ትመላሽ ታደርጋለች የሚል ሀሳብ የለም” ብለዋል፡፡
በ2024 መጀመርያ ወር ላይ ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገው የነበሩት ፖል ካጋሚ ስደተኞቹ ወደ ሩዋንዳ የማይመጡ ከሆነ ገንዘቡን ትመልሳላችሁ ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር፤
“ፕሬዝዳንቱ በምላሻቸው ለቅድመ ዝግጅት ወጪዎች በርካታ ገንዘቦችን ፈሰስ አድርገናል። ስደተኞቹ የማይመጡ ከሆነ ገንዘቡን እንመልሳለን ነገር ግን የምንገደድበት አሰራር የለም” ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር የስደተኞች እቅድ “ማታለያ ሀሳብ” በሚል የጠሩት ኪር ስታርመር የድንበር ላይ ቁጥጥሮችን ማጥበቅ እና ስደተኞች በህጋዊ መንገድ የሚገቡባቸውን አማራጮች ማስፋት ፓርቲያቸው በመፍትሄነት የሚተገብረው ጉዳይ መሆኑን ቃል ገብተዋል፡፡