ካማላ ሀሪስ "በምርጫ ስንሸነፍ ውጤቱን መቀበል የዲሞክራሲ መሰረታዊ መርህ ነው" ብለዋል
በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራችን በመወከል ሲወዳደሩ የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ የምርጫውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበሉ አስታወቁ።
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፕብሊካን እጩ የሆኑት እና የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ዳግም ወደ ስልጣን ተመልሰዋል።
ይህንን ተከትሎም ከትራምፕ ጋር ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በሃዋርድ ዩኒቨርቲ በምርጫው መሸነፋውን መቀበላቸውን አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል።
ለምርጫው ውጤት እውቅና የሰጡት ካማላ ሀሪስ፤ “ውጤቱ እኛ የምንፈልገው አይደለም፤ ነገር ግን ተስፋ እስካልቆረጥን እና እስከታገልን ድረስ የአሜሪካ የተስፋ ብርሃን ምንጊዜም ብሩህ ይሆናል" ብለዋል።
ከተመራጩ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በስልክ መወያየታቸውን ያስታወቁት ሀሪስ፤ “ዶናልድ ትራምፕን እንኳን ደስ አለህ ብዬዋለሁ፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር አብረን እንደምንሰራ ተነጋግረናል” ሲሉም አስታውቀዋል።
ካማላ ሀሪስ በንግግራቸው ለዶናልድ ትምፕ መልካም የስልጣን ዘመን ተመኝተዋል።
"በምርጫ ስንሸነፍ ውጤቱን መቀበል የዲሞክራሲ መሰረታዊ መርህ ነው" ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በንግግራቸው።
አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈዋል።
ምርጫውን ለማሸነፍ እጩዎች ቢያንስ 270 እና ከዛ በላይ የመራጭ ወኪሎችን ድምጽ ማግኘት ግዴታ ሲሆን፤ ዶናልድ ትራምፕ 294 ድምጽ በማግኘት ምርጫውን አሸንፈዋል።
ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፤ ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደ ተመሳሳይ ምርጫ በጆ ባይደን ተሸንፈው ስልጣን አስረክበው ነበር።
በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ምርጫ ታሪክ ዶናልድ ትራምፕ በተከታታይ መምራት ያልቻሉ እና ዳግም በመወዳደር ፕሬዝዳንት መሆን የቻሉ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ሆነዋል ሲል ኤፒ ዘግቧል።
ምክትላቸው ጄቫንስ ደግሞ የአሜሪካ 50ኛው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።