የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በእስያ ለሚያደርጉት ጉብኝት ሲንጋፖር ገብተዋል
ከሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ-ሂስያን ሉንግ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ይመክራሉም ነው የተባለው
ሃሪስ ጉብኝቱን “የቻይና ኃያልነትና ተጽእኖ በተመለከተ የአሜሪካ አቋም ለማሳወቅ ይጠቀሙበታል” ተብሏል
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በእስያ ለሚያደርጉት ጉብኝት ሲንጋፖር መግባታቸው ተሰማ፡፡
በሲንጋፖር የሚገኙት ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ቬትናምን ጨምሮ በተለያዩ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሃገራት ጉብኝት ያደርጋሉ ነው የተባለው፡፡
ሲንጋፖር በደረሱ ጊዜ በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቭያን ባላክሪሽናን አቀባበል እንደተደረገላቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካማላ ጉብኝቱን “አሁን ላይ በቀጠናው እያደገ የመጣውን የቻይና ኃያልነትና ተጽእኖ በተመለከተ የአሜሪካ አቋም ለማሳወቅና ለመወያየት ይጠቀሙበታል” ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በነገው እለተ ሰኞ ከሲንጋፖር ፕሬዝዳንት ሃሊማህ ያኮፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ-ሂስያን ሉንግ ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ ጋዜጣዊ መግለጫንም ይሰጣሉ ተብሏል፡፡
ሲንጋፖር በምትገኘው የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ ሆነው ንግግር እንደሚያደርጉ የሚጠበቁት ሃሪስ ማክሰኞ አመሻሽ ወደ ቬስትናም የሚያቀኑም ይሆናል፡፡
የምክትል ፕሬዝዳንቷ ጉዞ አሜሪካ በአፍጋኒስታን ጉዳይ በተጠመደችበት ወቅት መሆኑ አስቸጋሪ ሳይሆን እንደማይቀርም በርካታ ሃሳቦች በመሰንዘር ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ እንደምክንያትነት የሚያስቀምጡት ደግሞ አሁን አሜሪካ ጦሯን ከአፍጋን እያስወጣች ያለችበት ሂደት እ.ኤ.አ በ1975 በሳይጎን ከወሰደችው ተመሳሳይ እርምጃ ጋር በማነጻጸር ነው፡፡
ሃሪስ በኤስያ የሚያደርጉት ጉብኝት በሰኔ ወር ጓቲማላን እና ሜክሲኮን ከጎበኙ ወዲህ እያደረጉት ያለ ሁለተኛው የውጭ ጉብኝት ነው፡፡