“የአብርሃም ስምምነትን” ተከትሎ እስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር እንዲያደርጉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አሳሰቡ
ከዩኤኢ ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት እስራኤል የዌስት ባንክን ግዛቶች የመቆጣጠር እቅዷን መሰረዟ ይታወቃል
ስምምነቱ ለፍልስጤም እና እስራኤል ችግር መፍትሔ ለማምጣት እንደሚረዳ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል
“የአብርሃም ስምምነትን” ተከትሎ እስራኤል እና ፍልስጤም ድርድር እንዲያደርጉ የተመድ ዋና ጸሐፊ አሳሰቡ
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በእስራኤል እና በሁለት የባህረ ሰላጤው የአረብ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የዲፕሎማሲ ስምምነት ተከትሎ እስራኤል እና ፍልስጤማውያን እድሉን ለድርድር እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ፍልስጤማውያን ለወደፊቱ ሀገራቸው የሚፈልጉትን ግዛት ለመቆጣጠር እስራኤል የያዘችውን ዕቅድ እንድታቋርጥ ማድረጉን ጉተሬዝ እንደ መልካም ዕድል አንስተውታል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ቀጥታ ግንኙነትን ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ከሚሰሩ አካላት ሁሉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በማድረግ ላይ እየሰራ እንደሚገኝም ነው ዋና ጸሐፊው ያነሱት፡፡
“እስካሁን ድረስ ለመፍትሔው መግባባት ላይ መድረስ ባንችልም ፣ ጥረታችንን ግን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡ “በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ሂደት ዙሪያ ተስፋ አለመቁረጥ በጣም አስፈላጊ ነው” ማለታቸውንም ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ አደራዳሪነት ስምምነቶች እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከባህሬን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ የደረሰችውን የሰላም ስምምነት የተባበሩት መንግስታት እንደሚደግፍ በድጋሚ የገለጹት ጉተሬዝ “ችግሮችን ለመፍታት ዓለም አቀፍ መተባበር ፍጹም አስፈላጊ ነው ፡፡ ”በማለት ተናግረዋል፡፡
የሠላም ስምምነቶቹን ማክሰኞ ዕለት መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም በዋይት ሀውስ በነበረ ስነ ሥርዓት ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተፈራርመዋል፡፡
የእስራኤል ግዛት የማስፋፋት ድርጊት የሁለት ሀገር መፍትሔን እንደሚቃረን ሁል ጊዜ ስናነሳ ነበር ያሉት ጉተሬዝ እስራኤል ፍልስጤማውያን የኛ ነው የሚሉትን የዌስት ባንክን መሬት ለመጠቅለል ይዛው የነበረውን አከራካሪ እቅዷን እንድታቆም በሚጠይቀው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ስምምነት ላይ አተኩረዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት እስራኤል የዌስት ባንክን ግዛቶች የመቆጣጠር እቅዷን መሰረዟ ይታወቃል፡፡