ዮቭ ጋላንትን ያባረሩት ኔታንያሁ አዲስ የመከላከያ ሚኒስትር ሾሙ
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሀላ ፈጽመዋል
ካትዝ የመጨረሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸው እስራኤልና ፈረንሳይን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ በመክተት ተጠናቋል
እስራኤል አዲስ የመከላከያ ሚኒስትር ሾማለች።
የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ አዲሱ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ትናንት በፓርላማ በመገኘት ቃለመሃላ ፈጽመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ባለፈው ማክሰኞ ዮቭ ጋላንትን ከሃላፊነታቸው ማሰናበታቸው ይታወሳል።
የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል በጋዛም ሆነ በሊባኖስ ግቧን አሳክታለች፤ በሁለቱም ጦሯን ማቆየቷ ፋይዳ የለውም የሚል አስተያየት መስጠታቸው በተነገረ ማግስት ነው የተባረሩት።
ኔታንያሁ ድህረ ጋዛ ጦርነት እቅድ የላቸውም የሚለው የቀደመ አስተያየታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዳጋጫቸው የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የጋላንት እና ኔታንያሁን ግንኙነት ያሻገረው ጉዳይ “አልትራ ኦርቶዶክስ አይሁዶች” በእስራኤል ጦር እንዳይካተቱ መደረጉ ነው።
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር በእስራኤል ጦር ውስጥ የእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችን መካተት ይደፍፋሉ፤ ኔታንያሁ ደግሞ የጥምር መንግስታቸው ላይ አደጋ እንደሚደቅን በመጥቀስ ክልከላው እንዲቀጥሉ ይሻሉ።
የእስራኤል የተቃዋሚ ፖለቲከኞች እስራኤል በጦርነት ውስጥ ባለችበትና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የታገቱ እስራኤላውያን እንዲለቀቁ በተቃውሞ ሰልፎች የቴል አቪቭን ጎዳና ባጨናነቁበት ወቅት ኔታንያሁ ጋላንትን ማባረራቸውን ተቃውመዋል።
ጋላንትን የተኩት እስራኤል ካትዝ የኔታንያሁ የረጅም ጊዜ ወዳጅ መሆናቸውንና “የእስራኤል ጠላቶችን” ለማጥፋት በተደጋጋሚ በመዛት እንደሚታወቁ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የካትዝ የመጨረሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የስልጣን ቆይታ እስራኤልና ፈረንሳይን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ከቶ ነበር።
የእስራኤል ፖሊስ በእየሩሳሌም በሚገኝ የፈረንሳይ ቤተክርስቲያን በመግባት ሁለት የጸጥታ ሃይሎችን መቆጣጠሩ ፓሪስን አስቆጥቷል።
ድርጊቱ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄን ኖል ባሮት በቤተክርስቲያኑ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት እንዲሰርዙ አድርጓል።
ሚኒስትሩ ከካትዝ ጋር ባለፈው ሃሙስ በሰጡት መግለጫ እስራኤል በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ መከልከሏ እና በሰሜን ጋዛ የአየር ድብደባዋን መቀጠሏ ለቀጣይ ደህንነቷ አስጊ ነው ብለዋል።
አዲሱ መከላከያ ሚኒስትር በሊባኖስ ከሄዝቦላህ፤ በጋዛ ከሃማስ ጋር የተጠናከረውን ጦርነት የመምራት ከፍተኛ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።