ካዛኪስታን የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ህዝበ ውሳኔ እያካሄደች ነው
በህዝበ ውሳኔው የሀገሪቱ ዜጎች ድጋፍ ከሰጡ የሩሲያው ሮሳቶም የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫውን ይገነባዋል ተብሏል
የማዕከላዊ እስያዊቷ ሀገር ከአለማችን ከፍተኛ የዩራኒየም አምራች ሀገራት መካከል አንዷ ናት
ካዛኪስታን የመጀመሪያውን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ለመገንባት ባቀረበችው ሀሳብ ላይ ዜጎቿ ድምጽ እንዲሰጡበት እያደረገች ነው።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ካሳይም ጆማርት ቶካየቭ በካይ የድንጋይ ከሰል ሃይል ማመንጫዎችን ለመተካት የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ የመገንባቱን ሀሳብ አቅርበዋል።
በዛሬው እለት ዜጎች ድምጽ እየሰጡበት ያለው ህዝበ ውሳኔ በአብላጫ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነም የሩሲያው ሮሳቶም የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫውን ይገነባዋል ተብሏል።
የካዛኪስታን ካቢኔ ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሚሆነውን የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ኡልከን በተባለ ስፍራ እንዲገነባ ማቀዱንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
20 ሚሊየን ህዝብ ያላት ካዛኪስታን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ቢኖራትም አብዛኛውን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍላጎቷን የምታሟላው በድንጋይ ከሰል በሚሰሩ የሃይል ማመንጫዎች ነው።
ከሩሲያ ኤሌክትሪክ የምትገዛው የማዕከላዊ እስያ ሀገር በካይ ከሆነው ድንጋይ ከሰል ወደታዳሽ ሃይል አማራጮች ፊቷን በማዞር መሆኗን ገልጻለች።
ካዛኪስታን ከአለማችን ከፍተኛ ዩራኒየም አምራች ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ፕሬዝዳንት ቶካየቭ ከህዝበ ውሳኔው በፊት “ከአለም እድገትና ፍላጎት ጋር ራሳችን ለማስተካከል የተሻለ ተፎካካሪ የሚያደርገንን አማራጭ መጠቀም ይኖርብናል” ብለዋል
የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት አካል የዩራኒየም ሀብቷ ከፍተኛ ቢሆንም ማዕድኑን ሃይል ለማመንጨት በሚያስችል መልኩ የማብላላት አቅም አልገነባችም።
በሩሲያው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ገንቢ ተቋም ሮስታም እንዲገባ ለታቀደው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ከ10 እስከ 12 ቢሊየን ዶላር ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል ተገምቷል።
ተቺዎች ወጪው ከፍተኛ መሆኑንና የሶቪየት የኒዩክሌር ጠባሳ ባልለቀቃት ሀገር የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ መገንባት አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።
በፈረንጆቹ 1986 የቾርኖብል የኒዩክሌር ቀውስ ሲከሰት የሶቪየት ህብረት አካል የነበረችው ካዛኪስታን በመቶዎች የሚቆጠሩ የሶቪየት የኒዩክሌር መሳሪያዎች መሞከሪያ ጣቢያዎች የሚገኙባት ናት።
የኒዩክሌር መሞከሪያ ስፍራዎቹ በርካቶችን ለጤና ችግር ዳርገው ነዋሪዎችን ከቀያቸው ማፈናቀላቸውን የሚያወሳው የሬውተርስ ዘገባ፥ ማንኛውንም ከኒዩክሌር ጋር የተያያዘ ጉዳይ የሚፈሩ ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑንም ያብራራል።