ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ምርጫ በፊት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል ደቡብ ኮሪያ አስጠነቀቀች
ዩን ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር የሰሜን ኮሪያን እንቅስቃሴ እየተከታተለች ነው ብለዋል
ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ ሉአላዊነት የሚጣስ ከሆነ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ተጠቅመው ደቡብ ኮሪያን አጠፋለሁ ሲሉ ባለፈው ሳምንት ዝተዋል
ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ምርጫ በፊት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል ደቡብ ኮሪያ አስጠነቀቀች።
የደቡብ ኮረያ ፕሬዝደንት ዩን ሱክ የኦሎ በትናንትናው እለት ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የኑክሌር ጣቢያዎቿን ያሳየችው ከህዳሩ ምርጫ ወዲህ የዋሽንግተንን ትኩረት ለመሳብ ነው ብለዋል።
"ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የኑክሌር ጣቢያዎቿን ያሳየችው ከአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫው በፊት የአሜሪካን እና የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ ነው፤ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር እና የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ በማድረግ ተጨማሪ ትንኮሳ ልትፈጽም ትችላለች" ብለዋል ዩን።
ሰሜን ኮሪያ ሚስጥራዊ የተባለውን የዩራኒየም ማብላያ ጣቢያዋን ማሳየቷን እና ተጨማሪ የኑክሌር መሳሪያዎች እንደምታመርት መዛቷን ተከትሎ ባለፉት ሳምንት ውስጥ በሰሜን ኮሪያ ዙሪያ ያለው ስጋት እያደገ ነው።
ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ ሉአላዊነት የሚጣስ ከሆነ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ተጠቅመው ደቡብ ኮሪያን አጠፋለሁ ሲሉ ባለፈው ሳምንት ዝተዋል።
በርካታ የውጭ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አቅሟን ማዕቀብ እንዲነሳላት ለማድረግ እንደመደራደሪያ ልትጠቀምበት ትችላለች ይላሉ።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ኪም ከዲሞክራቷ እጩ ካማላ ሀሪስ ይልቅ ከ2018-19 በተካሄደው የኑክሌር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ያነጋገራቸው ትራምፕ ማሸነፍ የሚፈልጉትን ለማግኘት የበለጠ እድል እንደሚሰጣቸው ያስባሉ።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ትራምፕ ከኪም ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲያወድሱ ሀሪስ ግን እንደ ኪም ያሉ አምባገነኖችን እንደማያባብሉ ተናግረዋል።
ኪም ባለፈው ወር የኑክሌር ጣቢያቸውን ይፋ ማድረጋቸው ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ፕሮግራሟን እንድታጠፋ በአሜሪካ መሪነት ለሚደረገው ጥረት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ዩን ፒዮንግያንግ ለኑክሌር እና ለባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ መዘጋጀቷን የሚያሳይ ምልክት ስለማግኘታቸው አላብራሩም። ዩኖ አክለውም ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር የሰሜን ኮሪያን እንቅስቃሴ እየተከታተለች ነው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ ስድስት የመሬት ስር የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ያደረገች ሲሆን በቅርብ አመታት ደግሞ ብዙ የባለስቲክ ሚሳይል ሙከራዎ አድርጋለች።
የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካን ጥምረት በስጋት የምትመለከተው ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸጓን እንደምትቀጥል ደጋጋግማ አረጋግጣለች። ደቡብ ኮሪም፣ ሰሜን ኮሪያ በኑክሌር ጥቃት ከከፈተችባት የምትሰጠው ምላሽ የከፋ እንደሚሆን ዝታለች።