የሩሲያን የኒዩክሌር መሳሪያ አጠቃቀም የሚወስነው ህግ እየተሻሻለ ነው - ፑቲን
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ እና ብሪታንያ ለዩክሬን የላኳቸው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ሩሲያን ከመቱ የኒዩክሌር መሳሪያዎቻችን እንጠቀማለን ሲሉ ዝተዋል
ኬቭ በበኩሏ “ሩሲያ አለምን በኒዩክሌር ከማስፈራራት ውጭ አማራጭ የላትም” ብላለች
ሩሲያ በምዕራባውያን ኮንቬንሽናል ሚሳኤሎች ጥቃት ከደረሰባት የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ለመጠቀም ትገደዳለች አሉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን።
ሞስኮ ከባለፈው አመት ጀምሮ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መቼና እንዴት መጠቀም እንዳለባት የሚወስነውን ህጓን በማሻሻል ላይ መሆኗንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።
ፑቲን የሀገሪቱ የደህንነት ምክርቤት ስብሰባን ሲከፍቱ የኒዩክሌር ህጉን ማሻሻል ያስፈለገው ሞስኮ ለተደቀነባት አደጋ ምላሽ ለመስጠት ነው ብለዋል።
ማሻሻያው ኒዩክሌር ያልታጠቁ ሀገራት ከታጠቁት ጋር በመተባበር በሩሲያ ላይ ጥቃት ካደረሱ በሞስኮ ላይ “የጋራ ጥቃት” እንደከፈቱ ይቆጠራል የሚል ሃሳብ ማካተቱንም ተናግረዋል።
ሩሲያ የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መቼ መጠቀም እንዳለባት በግልጽ መስፈሩን በማንሳትም ከፍተኛ ድንበር አቋራጭ የሚሳኤል፣ የአየር እና ድሮን ጥቃት ከተፈጸመ ሀገራቸው አውዳሚዎቹን መሳሪያዎች መጠቀም እንደምትጀምር አብራርተዋል።
ሞስኮ አጋሯ ቤላሩስ ከተወረረች እና በኮንቬንሽናል መሳሪያዎች ጥቃት ከደረሰባት የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን ልትጠቀም እንደምትችል መናገራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ሩሲያ በ2020 በይፋ ያወጣችውን የኒዩክሌር ህግ እያሻሻለች መሆኑን ያስታወቀችው አሜሪካ እና ብሪታንያ ለዩክሬን የላኳቸው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለማሳሰብ ነው ተብሏል።
በአሜሪካ የሚገኙት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ረጅም ርቀት የሚጓዙትን ሚሳኤሎች በመጠቀም ሩሲያን እንድትመታ ፈቃድ እንዲሰጧቸው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል።
ኬቭ ከዋሽንግተንም ሆነ ለንደን ፈቃድ ካገኘችና ሚሳኤሎችን ወደ ሞስኮ መተኮስ ከጀመረች ሶስተኛውና የኒዩክሌር ጦርነት ሊጀመር ይችላል የሚሉ ተንታኞች፥ የኬቭ አጋሮች ይህን አደገኛ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ ይናገራሉ።
የዩክሬን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አንድሪ ያምራክ ግን “ሩሲያ አለምን በኒዩክሌር ከማስፈራራት ውጭ አማራጭ የላትም” ሲሉ ለፑቲን ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሩሲያ በኒዩክሌር ጦር መሳሪያ አቅም የአለማችን ቀዳሚዋ ሀገር ናት።
በአለም ላይ ከተመረቱ የኒዩክሌር አረሮች 88 በመቶው በሩሲያ እና አሜሪካ ነው የሚገኘው።
“ኒዩክሌር የዜጎቻችን ደህንነት ለማስጠበቅም ሆነ የአለም ስርአት ሚዛንን ለማስተካከል ዋነኛው አማራጭ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፥ ምዕራባውያን ሀገራት “በእሳት እንዳይጫወቱ” አሳስበዋል ተብሏል።