የማራቶን አትሌቶች አሰልጣኝ የሆኑት ገመዶ ደደሮ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደ የሽልማት ስነ ሰርአት ላይ ላሳዩት ተግባር ይቅርታ ጠየቁ
ሸልማት የመለሱት አሰልጣኝ ገመዶ ደደፎ ይቅርታ ጠየቁ።
የማራቶን አትሌቶች አሰልጣኝ የሆኑት ገመዶ ትናንት ምሽት በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደ የሽልማት ስነ ሰርአት ላይ ላሳዩት ተግባር ይቅርታ ጠይቀዋል።
አሰልጣኙ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "በስሜታዊነት ላደረኩት ንግግር" ህዝብን እና ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ይቅርታ እየጠይቃለሁ ብለዋል።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልኡክ በተዘጋጀው የአቀባበል እና የእውቅና ስነስርአት ላይ አሰልጣኙ ሽልማቱን ከፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ተቀብለው መጠኑን ካዩ በኋላ የሁለት ሚሊዮን ሸልማት "ለእኔ ስድብ ስለሆነ መመለስ እፈልጋለሁ፤ የሚመጣውን ሁሉ እቀበላለሁ" በማለት መመለሳቸው ነው ትችት ያስነሳባቸው።
“ክብርት ፕሬዝዳንታችን እኛ አሰልጣኞች ለረጅም ጊዜ ለፍተናል፣ለረጅ ጊዜ ትልቅ ነገር አድርገናል፤ ልፋታችንን አይመጥንም” ነበር ያሉት አሰልጣኙ።
አሰልጣኝ ገመዶ "ይቅርታውን ህዝቤ እንዲቀበለኝ፣ 1500፣ በ5ሺ እና በ10ሺ ለጠፋው ውጤት የእኛ የአሰልጣኞች እጅ አለበት። የአሰራርም እና የአትሌቶችም ችግር አለበት፤ ህዝባችንን በውጤት ለመካስ ቃል እገባለሁ። ስሜታዊ ሆኜ ላጠፋሁት ጥፋትም ህዝቤ እንዲገነዘበኝ እፈልጋሉሁ" ብለዋል።
አሰልጣኝ ገመዶ ይቅታ የጠየቁት በሰነስርአቱ ወቅት ላሰሙት ንግግር ብቻ ነው።
በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው ታምራት ቶላ እና የብር ሜዳሊያ ያመጣችው አትሌት አሰልጣኝ የሆኑት ገመዶ፣ ለአሰልጣኝ የተሰጠው ክብር ዝቅ ያለ መሆኑን እና ይህ አሁንም ቅር እንዳሰኛቸው አልሸሸጉም።
አሰልጣኙ ሽልማቱን ያዘጋጀውን የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ይቅርታ እንደማይጠይቁ እና ሌሎች አሰልጣኞችም በሚስቴሩ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በሽልማቱ ስነ ስርአቱ የኢትዮጵያ የፓሪሶ ኦሎምፒክ ልኡኳን እንደየተሳትፏቸው ከ50ሺ ብር ጀምሮ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በማራቶን ለኢትዮጵያ ብቸኛውን ወርቅ ሜዳሊያ ላስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ 7 ሚሊየን ብር እና ወርቅ ኒሻን ሽልማት ተበርክቶለታል።የብር ሜዳልያ ላመጡት አትሌት ትግስት አሰፋ፣ አትሌት በሪሁን አረጋዊ እና አትሌት ፅጌ ዱጉማ ለእያንዳንዳቸው የ 4 ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል።
በኦሎምፒክ መድረኮች በሚካሄዱ የመካከለኛ ርቀት ሩጫ የበላይነት ይዘው ያጠናቅቁ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድሮ አልተሳካላቸውም።