የስራ ማቆም አድማ ወደ ኬንያ መዲና የሚደረጉ በረራዎችን አስተጓጎለ
የኢትዮጵያ አየርመንገድን ጨምሮ የተለያዩ አየርመንገዶች መነሻና መዳረሻቸውን ናይሮቢ ያደረጉ በረራዎች በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን እየገለጹ ነው
አውሮፕላን ማረፊያውን የህንዱ አዳኒ ግሩፕ በሊዝ እንዲያስተዳድረው መታቀዱ ቁጣ አስነስቷል
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚያደርገውን በረራ በጊዜያዊነት ማቋረጡን ገለጸ።
አየርመንገዱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግላጫ በረራው የተቋረጠው በጄሞ ኬንያታ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው ነው።
የሰራተኞቹ አድማ ወደ ናይሮቢ የሚደረግም ሆነ ከናይሮቢ የሚነሱ በረራዎች ላይ ተጽዕኖ ማድረጉን ነው አየርመንገዱ ባወጣው መግለጫ የጠቆመው።
ለተፈጠረው የመንገደኞች መንገላታት ይቅርታ የጠየቀው አየርመንገዱ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም አስታውቋል።
የኬንያ ኤርወይስም መነሻና መዳረሻቸውን ናይሮቢ የሚያደርጉ በረራዎች ሊዘገዩ አልያም ሊራዘሙ እንደሚችሉ ገልጿል።
የኬንያ አቪየሽን ሰራተኞች ማህበር የጠራውን የሰራ ማቆም አድማ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው ተብሏል።
አድማውን ተከትሎም በኬንያ ዋነኛው አውሮፕላን ማረፊያ በረራዎች ተስተጓጉለው በርካታ መንገደኞችም ከአውሮፕላን ማረፊያው ውጭ ሆነው የአድማውን ማብቂያ እየተጠባበቁ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የአቪየሽን ሰራተኞች ማህበሩ አድማው የኬንያ መንግስት የጀሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያን ለህንዳዊው ቢሊየነር ጓታም ሃዳኒ ኩባንያ “አዳኒ ግሩፕ” በሊዝ ለመሸጥ የያዘውን እቅድ እስኪሰርዝ ድረስ ይቀጥላል ማለቱንም ነው የኬንያ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ የሚገኙት።
የኬንያ መንግስት አዳኒ ግሩፕ ለ30 አመታት አውሮፕላኑን ሲያስተዳድር በምትኩ የ1 ነጥብ 85 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ያገኛል ተብሏል።
የሰራተኞች ማህበሩ ግን አውሮፕላን ማረፊያውን አዳኒ ግሩፕ በሊዝ እንዲያስተዳድረው መፍቀድ ኬንያውያን ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ይነቅላል፤ የአውሮፕላኑን የወደፊት ትርፍም ይቀማል በሚል ተቃውሞታል።
የኬንያ ከፍተኛ ፍርድቤት “ግልጽነት ይጎድለዋል” ያለውን የሊዝ እቅድ እንዳይጸድቅ ያሳሰበ ቢሆንም የኬንያ መንግስት ግን አውሮፕላን ማረፊያውን ለማዘመን ወሳኝ ነው በሚል ሲሞግት ቆይቷል።
በ2022/23 8 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ መንገደኞች እና ከ380 ሺህ ቶን በላይ ጭነት ያስተናገደው የጀሞ ኬንያታ አለማቀፍ ኤርፖርት በአፍሪካ ስራ ከሚበዛባቸው አውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል አንዱ ነው።