አሜሪካ ፑቲን “እጅግ አደገኛ ችግር ይፈጥራል” ያሉትን ውሳኔ ልታሳልፍ ነው
ፕሬዝዳንት ባይደን ዩክሬን በአሜሪካ ሰራሽ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎች ሩሲያን እንዳታጠቃ ተጥሎ የቆየውን ክልከላ ለማንሳት እየተዘጋጀን ነው ብለዋል
ዋሽንግተን ክልከላዋን ካነሳች የኒዩክሌር ጦርነት ጅማሬ ይሆናል ስትል ሞስኮ አስጠንቅቃ ነበር
አሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኢሎቿ ሩሲያን ለማጥቃት እንዳይውሉ በዩክሬን ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ ልታነሳ እንደምትችል ፕሬዝዳንት ባይደን ፍንጭ ሰጥተዋል።
ክልከላው ከተነሳ የሩሲያን ግዛት አልፈው ጥቃት ማድረስ በሚችሉ ሚሳኤሎችን እንድትጠቀም ስትወተውት ለነበረችው ኬቭ ትልቅ ብስራት ይሆናል።
ዩክሬን የምዕራባውያን የጦር መሳሪያ ድጋፍ መዘግየትና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን እንዳትጠቀም የተጣሉባት ማዕቀቦች ለመልሶ ማጥቃቱ አለመሳካት በምክንያትነት ስታቀርብ መቆየቷ ይታወሳል።
ሩሲያ ባይደን ለሰጡት ፍንጭ እስካሁን ምላሽ ባትሰጥም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን አሜሪካ ውሳኔውን ካሳለፈች “እጅግ ከባድ ችግር ይፈጠራል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዩክሬን ላይ ተጥሎ የቆየው እገዳ እንዲነሳ መንግስታቸው እየሰራ መሆኑን የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ የኢራንን አጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤሎች ተቀብላለች ባሉ ማግስት ነው።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የኬቭ ዋነኛ አጋር ሆና በእጅ አዙር የተሰለፈችው አሜሪካ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎቿ ወደ ሩሲያ በጥልቀት ዘልቀው ጥቃት ለማድረስ እንዳይውሉ አግዳ ቆይታለች።
ክልከላውን ለማንሳት እንቅስቃሴዋ ሞስኮ ከቴህራን ባለስቲክ ሚሳኤሎች እያገኘች ነው የሚለው አንዱ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ባይደን በግልጽ አልጠቀሱም።
ዋይትሃውስ ቀደም ብሎም የዋሽንግተን አጭር ርቀት ሚሳኤሎች በሩሲያ ድንበሮች ጥቅም ላይ እንዲወሉ መፍቀዱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ባይደን ፍንጭ የሰጡበት ጉዳይ ውሳኔ ከተደረሰበት ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራትም ለኬቭ ያቀረቡት ሚሳኤል ጥቅም ላይ እንዲውል ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
ይህም አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በሞስኮ ላይ በቀጥታ ጥቃት እንደከፈቱና ጦርነት እንዳወጁ ይቆጠራል በሚል ፕሬዝዳንት ፑቲን በያዝነው አመት መጀመሪያ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።
የምዕራባውያን ሚሳኤሎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ከተፈጸመባቸው የጦርነቱን አድማስ እንደሚያሰፋውና “የኒዩክሌር ጦርነት” ሊጀምር እንደሚችልም ፑቲን ገልጸው ነበር።
ጥቃቱን ምንም እንኳን ዩክሬን ብታደርሰው ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ያስታጠቋት ሀገራት ሃላፊነቱን እንደሚወስዱም መናገራቸውም አይዘነጋም።