ልዩልዩ
ኬንያ አየር መንገድ ከአሁን በኋላ ዝንጀሮዎችን ወደ አሜሪካ አላጓጉዝም አለ
ዝንጀሮዎቹን ለማጓጓዝ የገባውን ውል እንደማያድስም አየር መንገዱ አስታውቋል
አየር መንገዱ ከእንስሳቱ አያያዝ ጋር በተያያዘ በተቆርቋሪዎች መወቀሱን ተከትሎ ነው ይህን ያለው
ኬንያ አየር መንገድ ከአሁን በኋላ ለላቦራቶሪ ምርምር የሚሆኑ የዝንጀሮ ዝርያዎችን ወደ አሜሪካ አላጓጉዝም አለ፡፡
ዝንጀሮዎቹ ሞውሪታኒያ ከሚገኝ የማዳቀያ ስፍራ ነው ወደ አሜሪካ የሚጓጓዙት፡፡
ሆኖም አየር መንገዱ ከአሁን በኋላ ዝንጀሮዎቹን አላጓጉዝም ብሏል፡፡ ከላኪ ድርጅቱ ጋር የገባውን የጉዞ ውል ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደማያድስም ነው ያስታወቀው፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ባሳለፍነው አርብ ባጋጠመ የተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝንጀሮዎች በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ ጎዳናዎች ተጉላልተዋል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው፡፡
አደጋው አየር መንገዱ አጓጉዞ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያደረሳቸው ዝንጀሮዎች ይጓዙበት በነበረው ተሽከርካሪ ላይ ነበር ያጋጠመው፡፡
ያን ተከትሎ ድርጊቱን የኮነኑት የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች አየር መንገዱን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ከረጅም የበረራ ሰዓታት በኋላ በቤተ ሙከራዎች ለእንግልትና ስቃይ እየተዳረጉ ላሏቸው ዝንጀሮዎች ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ነው አየር መንገዱ ኮንትራቱን እንደማያድስ ነው ያስታወቀው፡፡