በኬንያ የሚገኝውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተከትሎ ስርቆትን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች በ19 በመቶ መጨመራቸው ተነግሯል
በተያዘው አመት በኬንያ የተፈጸሙ እና ሪፖርት የተደረጉ ወንጀሎች አንድ መቶ ሽህ መሻገራቸው ሲገለጽ ይህም ከረጅም ጊዜ በኋላ የተመዘገበ ከፍተኛ የወንጀል ቁጥር መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
የሚፈጸሙት ወንጀሎች ማጭበርበር፣ ንጥቂያ፣ ስርቆት እና የቡድን ዝርፍያን የሚያካትቱ ናቸው፡፡
በሀገሪቱ የሚገኝው ከፍተኛ የስራ አጦች ቁጥር እና የዋጋ ንረት የዜጎችን የመገዛት አቅም በማዳከም ኑሯቸውን እንዳከበደው ይነገራል፡፡
የኬንያ ስታትስቲክስ ቢሮ ባወጣው መረጃ መሰረት ከግድያ ወንጀል በስተቀር በሀገሪቱ ሁሉም አይነት የስርቆት ወንጀሎች ተበራክተዋል፡፡
በ2022 በሀገሪቱ ይፈጸም የነበረው የግድያ ወንጀል ቁጥር ከ3056 ወደ 3031 ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በአንጻሩ የተደራጀ ዝርፍያ በ27 በመቶ ሲጨምር ስርቆት ደግሞ በ25.9 በመቶ አሻቅቧል፡፡
ናይሮቤ በ9.9 በመቶ የሚገኝውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደች ቢሆንም አሁንም ግን በሀገሪቱ የሚገኝውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በሚፈለገው ልክ ሊያሻሽለው አልቻለም፡፡
በሀገሪቱ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ስራ አጥ ሲሆን የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችም መንግስት የታክስ ጭማሪ ሊያደርግ ነው ከተባለ በኋላ የሰራተኛ ቅነሳ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የኬንያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የዊልያም ሩቶ መንግስት አደርገዋለሁ ያለው የታክስ ጭማሪ በሀገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በማባባስ ዜጎች ወንጀልን ችግራቸውን ለማስታገስ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማስጠንቀቁን ዘ ኢስት አፍሪካን አስነብቧል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚገኙ እስር ቤቶች የሚገኙ የእስረኞች ቁጥር በ46.3 በመቶ መጨመሩ ለዚህ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፡፡
አንዳንድ ወንጀሎችን የሚያከፋቸው ደግሞ በመንግስት ሰራተኞች እና ፖሊሶች ጭምር የሚፈጸሙ መሆናቸው ነው ብሏል ዘገባው። በተለይ በጎብኚዎች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ላይ ፖሊሶችም ተሳታፊ ናቸው ተብሏል፡፡ በባለፈው አመት 180 ፖሊሶች ተሳትፈውባቸዋል የተባሉ ወንጀሎች ሪፖርት ተደርገዋል፡፡
ከስርቆት ባለፈ ሀገሪቱን ህገ ወጥ የጦር መሳርያ ስርጭት እና የአደንዛዥ እጽ ዝውውርም ስጋት ሆኖባታል፡፡ በ2023 በኬንያ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር በ43 በመቶ ተመዝግቧል፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ሀገራቸው የምትገኝበትን ከፍተኛ የውጭ እዳ ጫና ለማቃለል፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናውን ለመከላከል እንዲሁም የስራ እድሎችን ለመፈጥር ከተለያዩ የአለም አቀፍም ገንዘብ አበዳሪዎች እና መንግስታት ጋር በመነጋገገር ላይ ናቸው፡፡